በጉራጌ ዞን በበጋ መስኖ እስካሁን ከ34 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል - ኢዜአ አማርኛ
በጉራጌ ዞን በበጋ መስኖ እስካሁን ከ34 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል
ወልቂጤ፣ ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)፡- በጉራጌ ዞን በዘንድሮ የበጋ መስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥ ከ34 ሺህ ሄክታር በላዩ በተለያዩ ሰብሎች እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ መልማቱ ተገለጸ።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ በዞኑ በዘንድሮ የበጋ ወራት የተለያዩ የውሀ አማራጮችና እርጥበትን በመጠቀም 62 ሺህ 184 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።
እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ ከ34 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ፣ ሽንብራ፣ በቆሎ፣ እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ መልማቱን ተናግረዋል።
ዘንድሮ በበጋ መስኖ ከሚለማው አጠቃላይ መሬት ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
የመስኖ ልማቱ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ገበያን ለማረጋጋት ታሳቢ በማድረግ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
አርሶ አደሩ ከልማቱ የተሻለ ምርት እንዲያገኝ የሙያ ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን አስታውቀዋል።
በዞኑ በእኖር ወረዳ ወርቃት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አህመዲን ጀማል በመስኖ በመታገዝ አንድ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ ሰብል እና አትክልት እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ከጓሮ አትክልት ምርት ሽያጭ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት አቅደው ልማቱን እያካሄዱ መሆናቸውን አመላክተዋል።
የመኸር ወቅት የበቆሎ ምርት በማንሳት በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ ሽምብራ መዝራታቸውን የገለጹት ደግሞ የአበሽጌ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሰብስቤ ተካ ናቸው።
እርጥበትን በመጠቀም ከዘሩት ሽምብራ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል።