የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በኋላ ዛሬ በስድስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ይመለሳል።
በዕለቱ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል።
የ16 ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ በስድስት ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያለው ሀዲያ ሆሳዕና በአራት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በአምስተኛ ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1 ለ 0 በማሸነፍ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ያገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
በአንጻሩ በአምስተኛ ሳምንት በሀላባ ከተማ የ2 ለ 1 ሽንፈት ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከመቻል ከቀኑ 10 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታም ተጠባቂ ነው።
ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ያገኘው ወልዋሎ በአንድ ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ወልዋሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ማጣሪያ ተሳትፎው ምክንያት ያላደረጋቸው ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች አሉት።
ተጋጣሚው መቻል በ10 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል።
ጨዋታው ወልዋሎ የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት፣ መቻል ደግሞ በአሸናፊነት ጉዞው ለመቀጠል የሚያደርጉት ነው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት እስከ ህዳር 13 2019 ዓ.ም ይቆያል።
የወላይታ ድቻው መሳይ ሰለሞን እና የባህር ዳር ከተማው አንተነህ ተፈራ በተመሳሳይ አምስት ጎሎችን በማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመሩ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ሄኖክ ኤርሚያስ በሶስት ግቦች ይከተላል።