ቀጥታ፡

ፎረሙ የአፍሪካ ምርቶች በዓለም ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እና የንግድ ልውውጥን ለማስፋፋት ወሳኝ ነው - ሚኒስትር ያስሚን ወሀብረቢ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2019(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ የንግድ ልማት ፎረም የአፍሪካ ምርቶች በዓለም ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ፣ የጥራት መሠረተ ልማትን ለማጠናከርና በአህጉሪቷ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማስፋፋት ወሳኝ መድረክ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሀብረቢ ገለጹ።

የአፍሪካ ሀገራትን የንግድ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ፣ የምርቶችን ጥራትና ደረጃ ለማረጋገጥ እንዲሁም የአህጉራዊ ገበያ ትስስርን ለማጠናከር ያለመው የአፍሪካ የንግድ ልማት ፎረም ህዳር 14 እና 15 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በትሬድ ማርክ አፍሪካ ትብብር የተዘጋጀው ፎረሙ “Building Africa’s Exports Through Quality” በሚል መሪ ሃሳብ ይካሃዳል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሯ ያስሚን ወሀብረቢ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ በፎረሙ ከ300 በላይ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪዎች፣ የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮች፣ የአህጉራዊና ቀጣናዊ ተቋማት ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶችና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች ይሳተፋሉ።

የአፍሪካ ምርቶች በዓለም ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ፣ የጥራት መሠረተ ልማትን ለማጠናከርና በአህጉሪቷ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማስፋፋት ወሳኝ መድረክ እንደሚሆንም ነው የገለጹት።

በፎረሙ የአፍሪካ ሀገራት በምርት ጥራት፣ በደረጃዎች ማጣጣም፣ በምርት ማረጋገጫና በገበያ ተደራሽነት ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን የሚመለከቱ ውይይቶች እንደሚካሄዱም አንስተዋል።

እንዲሁም የንግድ ማመቻቸት፣ የድንበር አስተዳደር፣ የገበያ ትስስርና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና (AfCFTA) አተገባበርን በተመለከተ ልምድና የመፍትሄ ሀሳቦች ይለዋወጣሉ ብለዋል።

በተጨማሪም የንግድ ልውውጥን የሚያግዙ የጥራት መሠረተ ልማቶችን፣ የላቦራቶሪ አቅምን፣ የምርት ማረጋገጫና የደረጃ አወሳሰን ሥርዓቶችን የሚመለከት የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) እና ትሬድ ማርክ አፍሪካ ጋር በትብብር የተዘጋጀ ሪፖርት በመድረኩ ይፋ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

የትሬድ ማርክ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴቪድ ቢር በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው እኤአ ከ2010 ጀምሮ በ23 የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ሥርዓትን ለማቀላጠፍ፣ ወጪና ጊዜን ለመቀነስ ከመንግሥታትና ከግሉ ዘርፍ ጋር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ ጋር ያላትን ትስስር ለማስፋትና የወጪ ንግዷን ለማሳደግ በምታደርገው ጥረት የፎረሙ መዘጋጀት የአፍሪካ ሀገራት በጋራ የንግድ እድሎችን እንዲጠቀሙና የአህጉራዊ ገበያ ትስስርን እንዲያጠናክሩ ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም