በሶማሌ ክልል በበጋ መስኖ ከ314 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማልማት ስራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል በበጋ መስኖ ከ314 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማልማት ስራ ተጀመረ
ጅግጅጋ፤ ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል በዘንድሮው የበጋ መስኖ ከ314 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የአነስተኛ መስኖ ልማት ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ሀሰን ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ለበጋ መስኖ ልማት ውጤታማነት በትኩረት እየተሠራ ነው።
በክልሉ ዘንድሮ በበጋ መስኖ ከ314 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
ከሚለማው መሬት ከ18 ሚሊዮን 660 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
የበጋ መስኖ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ የሚረዱና በጸሐይ ሃይል የሚሠሩ 198 የውሃ መሳቢያ ጀነሬተሮች ለአርሶ አደሮች መሰራጨታቸውን ገልጸዋል።
በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ከ543 ሺህ በላይ አርሶአደሮች እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።
በቢሮው የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ሥራ እስኪያጅ አቶ ዴክ ሁሴን በበኩላቸው በክልሉ ዘንድሮ በበጋ መስኖ ከሚለማው መሬት 12 ሺህ 600 ሄክታሩ በስንዴ እንደሚለማ ተናግረዋል።
ከስንዴ ልማቱ ከ293 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።
የስንዴ ምርታማነት ለማሳደግ ከምርምር ማእከላት የወጡ የተሻሻሉ ዝርያዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ አመልክተዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ በሸቤሌ፣ በሊበንና በአፍዴር ዞኖች የሚከናወን መሆኑን አስታውቀዋል።