ቀጥታ፡

የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ለአርሶ አደሮች የሚያደርገው ድጋፍ ምርትና ምርታማነታቸውን እያሳደገ ነው

ሆለታ፤ ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)፦ የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ባደረገልን የሥልጠና እና የእርሻ ሥራ ማሻሻያ ድጋፍ ምርትና ምርታማነታችንን ማሳደግ ችለናል ሲሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የአካባቢው አርሶ አደሮች እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም ባህላዊ አሠራርን እና ያልተሻሻሉ ዘሮችን በመጠቀም ዝቅተኛ ምርት ሲያገኙ ቆይተዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን ከማዕከሉ ባለሙያዎች ተግባራዊ ሥልጠና በመውሰድ፣ የባለሙያ ምክርን በመከተል እንዲሁም በሚያገኙት የምርጥ ዘር ድጋፍ ዘመናዊ ግብርናን በመተግበር ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በትክክለኛ የመሬት ዝግጅት፣ በወቅቱ በመዝራት፣ በማዳበሪያ አጠቃቀም እና በሰብል እንክብካቤ ላይ መሻሻል በመታየቱ በሄክታር የሚገኘው ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።

በአካባቢው ተጠቃሚ ከሆኑ አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ ቡዛየሁ በዬራ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ምርምር በማካሄድ አሲዳማ መሬቶችን በመለየት እና ለአሲዳማ መሬቶች ኖራ በማዘጋጀት ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ ሲያደርግላቸው ቆይቷል።

የማዕከሉ ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮች የሰጡት ሥልጠና ውጤታማ መሆኑን በመግለጽ፣ ቀደም ሲል በሰፊ መሬት ላይ አነስተኛ ምርት ያገኙ የነበሩትን በዚህ  ማዕከል ድጋፍ በአነስተኛ መሬት ላይ ከፍተኛ ምርት በማግኘት ኑሯቸውን እየለወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደር ገረመው ወልደሰማያት በበኩላቸው፣ ከማዕከሉ ያገኙትን ምክር በመከተል ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተለይም ቀደም ሲል  ምርት መስጠት አቅቶት የነበረው መሬታቸው በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ ባደረገው ድጋፍ ምርታቸው በእጥፍ መጨመሩንና ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በማዕከሉ የገብስ ሰብል ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ወንድሙ ፍቃዱ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ለረጅም ዓመታት በገብስ፣ በስንዴ፣ በድንች እና ሌሎች ሰብሎች ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር ሲያካሂድ ቆይቷል።

መንግሥት በሰጠው ትኩረት መሠረት ሀገሪቱ ለገብስ ምርት ምቹ በመሆኗ፣ የቢራ ገብስን ከውጭ ከማስገባት ይልቅ በሀገር ውስጥ በማምረት ለብቅል የሚያስፈልገውን የሀገር ውስጥ ፍላጎት ለማሟላት የሚሰራው ስራ ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።

በማዕከሉ የሰብል ምርምር የስራ ሂደት ተጠሪ እንዳሻው ግርማ እንደተናገሩት፣ የማዕከሉ ዓላማ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እና ዕውቀትን ማፍለቅ፣ ማሻሻል እና ያንን ተደራሽ ማድረግ ነው።

በዚህም የተለያዩ የግብርና ምርምሮችን በማካሄድ የምርምሩን ውጤት ወደ አርሶ አደሮች የማድረስ እና የግብርና ምርትን ለማሳደግ የባለሙያ ድጋፍ የመስጠቱን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም