ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ማመስገን እፈልጋለሁ- የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ልጅ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ማመስገን እፈልጋለሁ- የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ልጅ
የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ ሃውልት ትውልዱ ስራቸውን እንዲያውቅና እንዲነሳሳ የሚያደርግ ቋሚ መታሰቢያ ነውም ብለዋል።
በአዲስ አበባ 57 ሄክታር የሚሸፍን አዲስ የኮሪደር ልማት ሥራ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ትናንት ተመርቋል።በአዲስ አበባ ስታዲየም ጎን የኢትዮጵያ እግር ኳስ አባት ለሆኑት ለአቶ ይድነቃቸው ተሰማ የመታሰቢያ ሀውልት ቆሞላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ያደረጉት አስተዋጽኦ ትልቅ እና የሚታወቅ በመሆኑ፣ ለእሳቸው የሚገባውን ክብር መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።
እሳቸውን ማስታወስ መቻሉ ትልቅ ነገር እንደሆነና ለኢትዮጵያ ሰርተው ያገለገሉ ሰዎች እንዳይዘነጉ ምልክታቸውን በማስቀመጥ የሀገር ስም ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸው የመታሰቢያ ሀውልቱ መቆሙን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር የስልክ ቆይታ አድርገዋል።
ሃውልቱ ብዙ ህዝብ በሚሰባሰብበት እና በሚያምር ስፍራ በመገንባቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው አመልክተዋል።
አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ላለፉት 40 ዓመታት ሳይረሱ የቆዩ ቢሆንም፣ የሰው ልጅ ከትውልድ ትውልድ እየተረሳ ስለሚሄድ እንደዚህ ያለ ቋሚ መታሰቢያ መቆሙ ጠቃሚ መሆኑን አቶ ታደለ ጠቁመዋል።
እውቅናው በእግር ኳሱ በኩል ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተሰጠ ቢሆንም፣ ዋና አላማው ትውልዱ ይህ ሰው ማነው ብለው እንዲጠይቁ እና ከእግር ኳሱ ባለፈ ያሉትን ታሪኮች እንዲመረምሩና እንዲያውቁ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል።
ይህንን የመታሰቢያ ሃውልት ታሪክን ያከበረና ደግነት የተሞላበት መሆኑን አንስተዋል።
አንድ ሰው በህይወት ካለፈ ከ40 ዓመታት በኋላ የሚሰጥ እውቅና አክብሮቱ ለታሪክ መሆኑን ገልጸው፣ ተግባሩ እውቅና ሰጪውን የሚያስከብር እና ሌሎች በየዘርፉ እንዲተጉ የሚያበረታታ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ በየዘርፉ በርካታ ባለውለታዎች እንዳሏት የጠቆሙት አቶ ታደለ፣ የሁሉም ታሪክ እየተጠና ቢታወስ ለትውልድ አርአያ እንደሚሆን እና በስራ ላይ ያሉትንም እንደሚያነሳሳ ገልጸዋል።
የመታሰቢያ ሀውልቱ መቆም በእግር ኳስ አፍቃሪያን በአጠቃላይ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጠረው ደስታ እንዳስደሰታቸውና ኩራት እንዲሰማቸው ማድረጉን አመልክተዋል።
ሀውልቱ በስፖርት ቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን ከርቀት በፍቅርና በአክብሮት የሚከታተሉ ወዳጆችም የተደሰቱበት እና ከጠበቁት በላይ ምላሽ የተሰጠበት መሆኑን ገልጸዋል።
በግላቸው ከዚህ ቀደም መታሰቢያ መጠየቅ የእሳቸው ፋንታ እንዳልሆነና መታሰቢያ የመስጠት ሃላፊነት የሚመለከተው አካል መሆኑን የሚያምኑበት አቋም እንደነበራቸው ጠቅሰዋል።
መንግስታት በየዘመኑ የሰዎችን ታሪክ አጥንተው እውቅና መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል ሃውልቱ የፍላጎት መነሳሳትን እንደሚፈጥርና በተለይም ሰነዱንና ታሪኩን በያዙት ላይ ከባድ ሃላፊነት እንደሚጥል አቶ ታደለ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድም ከዚህ ሃውልት መነሻነት ታሪኩን በበለጠ ማወቅ ለሚፈልግ ሁሉ በየጊዜው የአባታቸውን ታሪክ ለማቅረብ እንዲተጉ ትልቅ ተነሳሽነት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
አቶ ይድነቃቸው በፍቅር ብቻ ተነሳስተው በተለያዩ ታሪካዊ ወቅቶች ከባዶ ተነስተው የስፖርት ኮሚሽን በማቋቋም ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከባቸውን አቶ ታደለ ገልጸዋል።
በሀገር ውስጥ የተለያዩ የስፖርት ስፍራዎችን በማስፋፋት የኢትዮጵያን ህዝብ የእግር ኳስና የኦሎምፒክ ወዳድ እንዲሆን ማድረጋቸውንና ከምንም ተነስቶም ሆነ በተሟላ ሁኔታ አቅዶ በመስራት ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አርአያ መሆናቸውን አመልክተዋል።
አቶ ታደለ ለሀገር ውለታ የዋሉ ሰዎች የማስታወስና እውቅና የመስጠት ተነሳሽነት ላላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፣ ሃውልቱ የተገነባበትን ውብና ህዝብ የሚሰባሰብበት ቦታ በመምረጣቸው ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጨምሮ ለሌሎች የመንግስት አመራሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።