ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ደኅንነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የጤና ጥናትና ምርምር ውጤቶችን እያፈለቀ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2019(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ደኅንነት ዘላቂነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የጤና ጥናትና ምርምር ውጤቶችን እያፈለቀ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ገለጸ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ!

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኖርዌይ በርገን እና ከታንዛንያ ሙሒምቢሊ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ብሔራዊ የሙያ ጤና ጉባኤ አካሂዷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ራሔል አርጋው በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ ጉባዔው ዩኒቨርሲቲዎቹ በሥራ አካባቢ ደኅንነት ዙሪያ በትብብር ያከናወኗቸውን ተግባራት በመገምገም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው።

ዩኒቨርሲቲው የሥራ ቦታ የጤና ስጋቶችን በመለየት በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረቱ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይም በኮንስትራክሽን፣ በግብርና፣ በማዕድንና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ያሉ የጤና ስጋቶችን የሚያመላክቱ ጥናቶች መካሔዳቸውን ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች፣ መሠረተ ልማቶችና አምራች ዘርፎች እየተስፋፉ በመሆናቸው፣ የሠራተኞችን የሥራ ቦታ ደኅንነት መጠበቅ ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሚከናወኑት ጥናትና ምርምሮች ለዘርፉ ፖሊሲ አውጪዎች በግብዓትነት እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል። 

የባለድርሻ ተቋማትን ቅንጅት በማጠናከር የፖሊሲዎች ግብዓትን በማፍለቅ በዘርፉ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብሮችን በመቅረጽ ብቁ የሙያ ጤንነት ባለሙያዎችን ማፍራት መቻሉንም አብራርተዋል።

በሥራ አካባቢዎች ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስም አሰሪዎችንና ሰራተኞችን በማወያየት፣ የሥራ ቦታዎችን በመጎብኘት እንዲሁም የማስተማርና የማማከር አገልግሎቶችን በመስጠት የመከላከልና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። 

ዩኒቨርሲቲው ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሥራ አካባቢ ደኅንነትን በዘላቂነት ለማስጠበቅ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሥራ በማከናወን ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የሙያ ጤንነትና ደኅንነት ፕሮጀክት ኃላፊ ፕሮፌሰር ዋቅጋሪ ዴሬሳ በበኩላቸው፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራትና የምርምር ሥራዎችን ማጠናከር ለሙያ ጤናና ደኅንነት መረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል። 

በፕሮጀክቶቹ አማካኝነትም የሙያ ጤና ማዕቀፍ መዘጋጀቱንና የላቦራቶሪ መሠረተ ልማቶች መጠናከራቸውን ተናግረዋል።

የኖርዌይ በርገን ዩኒቨርሲቲን በመወከል በመድረኩ የተገኙት ፕሮፌሰር ቤንቴ ሞዬን በበኩላቸው፤ የዩኒቨርሲቲዎቹ ትብብር ከተጀመረ ዐሥራ ሦስት ዓመታት መቆጠራቸውን ጠቅሰዋል።

በእነዚህ ዓመታት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጨባጭና ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል። 

በቀጣይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱን አጋርነትና ትብብር ይበልጥ በማጠናከር ለተሻለ ውጤት በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

"በጣም ጥሩ ትብብር እና ድንቅ ጊዜ ነበር። 13 ዓመታት መቆጠራቸው በራሱ አስደናቂ ነው። ኢትዮጵያ የ13 ወር የፀሐይ ጸጋ ባለቤት የሆነች ሀገር ናት፤ የእኛም ፕሮጀክት የ13 ዓመት የፀሐይ ብርሃን ሆኖ አልፏል። ይሁን እንጂ ገና ብዙ ሥራዎች ከፊታችን ይጠብቁናል።"

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም