ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን የደረሰ ሰብል በኮምባይነር ታግዞ እየተሰበሰበ ነው

ደብረ ማርቆስ፤ ሕዳር 10/ 2019 (ኢዜአ)--በምስራቅ ጎጃም ዞን በደረሰ ሰብል ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳያደርስና የምርት ብክነትን ለመቀነስ በኮምባይነር የታገዘ ምርት አሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ እምቢያለ አለኸኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደረስ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ምርት እየተሰበሰበ ነው።

በተለይም የአርሶ አደሩን ጊዜንና ጉልበት ለመቆጠብ እና የምርት ብክነትን ለመቀነስ የምርት አሰባሰብ ሥራው በኮምባይነር ታግዞ በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ ለምርት አሰባሰብ ስራው ከ95 በላይ ኮምባይነሮችን ለማስገባት መታቀዱንን ገልጸው፣ እስካሁንም ከ20 በላይ ኮምባይነሮች ገብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለሰብል ስብሰባ ሥራው ኮምባይነር ከመጠቀም በተጨማሪ አርሶ አደሩ በተለያዩ አደረጃጀቶቹ እና በደቦ ሰብሉን እየሰበሰበ መሆኑንም አቶ እምቢያለ አመልክተዋል። 

እስካሁን በተከናወነ የተቀናጀ እንቅስቃሴም ከ200 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት ሳይደርስበት ለመሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።

ቀሪውን የለማ ሰብል በፍጥነት የመሰብሰብ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያመለከቱት አቶ እምቢያለ፣  በየደረጃው ያሉ  የግብርና ባለሙያዎምች ለአርሶ አደን ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

በአዋበል ወረዳ የከይት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አራጋው ጌጡ በበኩላቸው እንዳሉት አንድ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ በኩታ ገጠም ያለሙትን  የስንዴ ሰብል በኮምባይነር ታግዘው  መሰብሰብ ችለዋል።

በዚህም  ምርታቸው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ለጉዳት እንዳይዳረገ መከላከል ከመቻላቸው በተጨማሪ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እንዳገዛቸው ገልጸዋል።

በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን የጤፍና ስንዴ ሰብል ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከልና ኮምባይነር እና የደቦ አሰራርን መጠቀማቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አርሶ አደር ይስማው ተገኝ ናቸው። 

ምስራቅ ጎጃም ዞን በመኽር ወቅቱ ከለማው ከ680 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከ25 ሚዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከግብርና ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም