በደቡብ ኦሞ ዞን 37 የመስኖ አውታሮች ተገንብተው ለአርብቶ አደሩ አገልግሎት እየሰጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኦሞ ዞን 37 የመስኖ አውታሮች ተገንብተው ለአርብቶ አደሩ አገልግሎት እየሰጡ ነው
ጂንካ፤ ሕዳር 10/2019 (ኢዜአ)፥ በደቡብ ኦሞ ዞን የአርብቶ አደሩን የመስኖ ተጠቃሚነት ለማሳደግ 37 አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ አውታሮች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ በተያዘው የበጋ ወቅት 32 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ምንላርገው አዲሱ ለኢዜአ እንደገለጹት የእንስሳት እርባታ ሥራ በስፋት በሚከናወንባቸው እንደ ደቡብ ኦሞ ባሉ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ጭምር የመስኖ ልማትን በማስፋፋት የህብረተሰቡን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
መንግሥት ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በሰጠው ትኩረት አርብቶ አደሩ ከከብት እርባታ ሥራው ጎን ለጎን በመስኖ ልማት እንዲሰማራ ማድረጉን ገልጸዋል።
በመስኖ ልማት የእርብቶ አደሩን ተጠቃሚነቱ ለማሳደግም 37 አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ አውታሮች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አቶ ምንላርገው አስታውቀዋል።
አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በመስኖ ልማት ሥራው የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባለፈ የገቢ አቅሙን እያሳደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
የመስኖ ልማቱም በተያዘው በጋ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት፣ በዚህም በመደበኛ ሰብል 16 ሺህ ሄክታር እንዲሁም በሆርቲካልቸር 15 ሺህ ሄክታር በማልማት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ከ35 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
ከዚሁ ጎን ለጎን ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑና ለኤክስፖርት የሚሆኑ የአትክልትና የቅባት እህሎችን በስፋት የማምረት ሥራ መከናወኑን ኃላፊው አመለክተዋል።
በዞኑ የኛንጋቶም ወረዳ ነዋሪ አርብቶ አደር ሎሞቶ ለዊኛ መንግሥት በመስኖ ልማት እንዲሳተፉ ባደረገላቸው ድጋፍ መሰረት የጀመሩት የማሽላ ልማት ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በከብት እርባታ ሥራው ብቻ ተሰማርተው እንደነበር አስታውሰው፣ የሰብል ልማት ሥራ መጀመራቸው ከምርቱ ሽያጭ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙና የሰብል ተረፈ ምርቱም ከብቶቻቸውን ለመመገብ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
ሌላው የወረዳው ነዋሪ ካፑል ሎሮሲያ በበኩላቸው የመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናችንን በማረጋገጥ ለኑሯችን መሰረትና መደላድል ሆኗል ብለዋል።
መንግሥት በመስኖ ልማት እንዲሰማሩ ባመቻቸላቸው ዕድል የኦሞ ወንዝን በመጥለፍ ማሳቸውን እያለሙና ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።