ቀጥታ፡

በጎንደር ጥንታዊ አብያተ መንግሥታት የሥነ-ሕንፃ ጥበብ ተደንቀናል- የውጭ ሀገር ጎብኝዎች

ጎንደር  ህዳር 10/2019(ኢዜአ) የጎንደርን ጥንታዊ አብያተ መንግሥታትን የጎበኙ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች፣ በቅርሶቹ የሥነ-ሕንፃ ጥበብ መደነቃቸውን ተናገሩ።

ለጉብኝት ጎንደር የተገኙት የውጭ ሀገር ዜጎች የጎንደር አብያተ መንግስታትን ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ የስነ ሕንፃውን ጥበብ አድንቀዋል። 

ሜክሲኳዊው ሚጌል ፓላስዮስ የጎንደርን ጥንታዊ አብያተ መንግሥታትን ሲጎበኝ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጿል።

የጎንደርን ጥንታዊ አብያተ መንግሥታት የሥነ ህንጻ ጥበብ ውብና የሚያስደንቅ ሆኖ እንዳገኘው ተናግሯል ።

ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶቹን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተደረገ ያለውን ጥረትም አድንቋል ።

ከሜክሲኮ ሲቲ የመጣችው አድሪያና ራሞስ በበኩሏ፤ በጎንደር ከተማ የመጀመሪያ ጉብኝቷ እንደሆነ ገልፃ በከተማው ጥንታዊና ታሪካዊ  ቅርሶች የተሰሩበት ጥበብ የሚደነቅ መሆኑን ገልጻለች።

ለቅርሶቹ አስፈላጎው እንክብካቤና እድሳት መደረጉን በጉብኝቷ መገንዘቧን ገልጻ ባየችው ነገር መደሰቷን ተናግራለች።

በጎንደር ከተማ የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት ያስደሰታቸው መሆኑን ጎብኝዎቹ ተናግረዋል ።

በጉብኝታቸው የተመለከቱትን ለሌሎች እንደሚያካፍሉም አስታውቀዋል።

በጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የቅርስ ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ አይቸው አዲሱ እንዳሉት፤ በበጀት አመቱ  ሦስት ወራት  ከ430 በላይ የውጭ እና ከ8 ሺህ 500 በላይ የሀገር ውስጥ ዜጎች በጎንደር ከተማ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል።

ታሪካዊ ቅርሶችን ጠብቆ ለማስቀጠል የጥገና እና የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም