ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከ28 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል - ኢዜአ አማርኛ
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከ28 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል
ሚዛን አማን፤ ህዳር 10/2019 (ኢዜአ)፦ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለፉት አራት ወራት ከ28 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ በላይ ኮጇብ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮ በጀት ዓመት ከ74 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለመላክ ታቅዶ እየተሠራ ነው።
በዚህም አስካሁን ድረስ ከ71 ሺህ 300 ቶን በላይ ቀይ እሸት ቡና መሰብሰቡንና 64 ሺህ ቶን ያህሉን ለማጠብ መቻሉን ተናግረዋል።
በክልሉ ካሉ 360 የቡና ኢንዱስትሪዎች መካከል 240 የቀይ እሸት ቡና ማጠቢያ ኢንዱስትሪዎች በቡና ምርት ዝግጅት በንቃት መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ያደረ የቡና ምርትን ጨምሮ አሟጦ በመሰብሰብ ለገበያ ለማቅረብ በተከናወኑ ሥራዎች ባለፉት 4 ወራት ጊዜ ውስጥ 28 ሺህ 358 ቶን የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
ለማዕከላዊ ገበያ ከቀረበው ውስጥ ከ4ሺህ 200 ቶን በላይ የሚሆነው የቡና ምርት የታጠበ ሲሆን ቀሪው ቅሽር ቡና መሆኑን አቶ በላይ ጠቁመዋል።
በክልሉ የቀይ እሸት ቡና ማጠቢያ ጊዜ በመጠናቀቁ ከተያዘው ኅዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ የጀንፈል ቡና አዘገጃጀት ላይ ሙሉ ለሙሉ ትኩረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን የሰሜን ቤንች ወረዳ አርሶ አደር ዘማች ቦይን ካላቸው ሦስት ሄክታር የቡና ማሳ እስከ 10 ኩንታል የቡና ምርት እንደሚሰበስቡ ተናግረዋል።
በጥራት የለቀሙትን ቀይ እሸት ለታጠበ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ከማቅረብ ጎን ለጎን በራሳቸው ጥራቱን የጠበቀ ደረቅ ቡና እያዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከአራት ሄክታር ማሳቸው10 ኩንታል ጥራት ያለው ቀይ እሸት ቡና ሰብስበው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ጌታቸው ዞላስ የተባሉ የወረዳው ነዋሪ ናቸው።
ከቡና ምርት ሽያጭ የሚያገኙትን ገቢ ለማሳደግ ለቡና ጥራት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ597 ሺህ 500 ሄክታር በላይ ማሳ በቡና የለማ መሆኑም ታውቋል።