ቀጥታ፡

በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራው ሥራ ውጤት ታይቷል ...የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ

ሲናና ህዳር 10/2019 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የምርጥ ዘር አቅርቦትን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት መታየቱን የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ገለጸ።

በኢንተርፕራይዙ የባሌ ቅርንጫፍ በሲናና እና በሮቤ እርሻ በመኽር ወቅትእያካሄደ ያለው የዘር ብዜት ልማት በባለድርሻ አካላት በመስክ ተጎብኝቷል።

የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጫላ አበበ በወቅቱ እንዳሉት ኢንተርፕራይዙ የምርጥ ዘር ምርትና አቅርቦትን ለማሻሻል ከግብርና ምርምር ተቋማትና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።

በተለይም ከምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በማስፋፋት፣ የዘር ጥራትን በማረጋገጥና የምርት ሂደቱን በማሻሻል ለአርሶ አደሩ የሚደርሰውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም ኢንተርፕራይዙ ባለፉት ዓመታት ባደረገው ጥረት የምርጥ ዘር አቅርቦትን ከማሻሻል ባሻገር የሰብል ምርታማነን በማሳደግ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን አመልክተዋል። 

የኢንተርፕራይዙን የምርጥ ዘር ልማት፣ የምርት ሂደትና ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚከናወኑ የትብብር ሥራዎችን ለመገምገም የተደረገው የባለድርሻ አካላት የመስክ ምልከታ የልማት ሥራዎቹን በተጨባጭ ለመመልከት ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

ኢንተርፕራይዙ በመኽር ወቅት እያለማቸው ያሉ ሰብሎች በጥሩ ቁመና ላይ ስለሚገኙ በቀጣይ የዘር አቅርቦት እጥረት እንደማያጋጥም አመላክተዋል። 

በኢንተርፕራይዙ የባሌ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን አስቻለው በበኩላቸው ቅርንጫፉ በመኽር ወቅቱ ከ16ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተለያዩ የሰብል ዘሮችን እያለማ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንተርፕራይዙ እያባዛቸው ከሚገኙ የሰብል ዘሮች መካከል የቢራ ገብስ፣ ስንዴ፣ ባቄላ፣ ጎመንዘር እንደሚገኙበት ጠቁመው ከልማቱ ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

በመስክ ምልከታው ከተሳተፉ ባለድርሻ አካላት መካከል የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዘላለም አለማየሁ በበኩላቸው የመስክ ምልከታው ኢንተርፕራይዙ የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር አቅርቦት ለማሻሻል እያከናወነ የሚገኘውን የዘር ብዜት የልማት ጥረት እንዲገነዘቡያስቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንዲሁም የምርጥ ዘር አጠቃቀም ግንዛቤን ለማሳደግና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጠናከር እንደሚረዳ አክለዋል።

ሌላው በመስክ ምልከታው ተሳታፊ የቦርትማልት ድርጅት ተወካይ አቶ ሱፊያን አማን በበኩላቸው ከኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር በሰፊ መሬት ላይ የቢራ ገብስ የምርጥ ዘር ልማትን ለማስፋፋት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። 

ከአርሶ አደሮች መካከል አቶ ሁሴን አህመድና ከድር ማህሙድ በበኩላቸው እንዳሉት ከኢንተርፕራይዙ በየጊዜው በሚያገኙት ምርጥ ዘር ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ሰራተኞች፣የግብርና ምርምር መዕከላት ተመራማሪዎች፣  አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም