ቀጥታ፡

ደህንነቱ የተጠበቀ የሰዎች እንቅስቃሴ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን፣ የክህሎት ልማትን፣ ሥራ ፈጠራን እና ቀጣናዊ ትስስርን ያጠናክራል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2019(ኢዜአ)፦ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ሥርዓት ያለው የሰዎች እንቅስቃሴ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን፣ የክህሎት ልማትን፣ ሥራ ፈጠራን እና ቀጣናዊ ትስስርን ያጠናክራል ሲሉ የኡጋንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቢናህ ናባንጃ ገለፁ።

የ2026ቱ የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት መድረክ በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ "የሰዎች እንቅስቃሴ ለቀጣናዊ ትስስር፣ ነፃ ዝውውር፣ ምቹ የሥራ ዕድል፣ ጥበቃ እና የጋራ ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል።

መርሃ ግብሩ የሰዎችን ክብር የሚጠብቅ፣ የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚከላከል እንዲሁም የሰዎች እንቅስቃሴ ለቀጣናዊ ትስስር፣ ለትብብርና ለጋራ ብልጽግና ወሳኝ አንቀሳቃሽ ኃይል መሆኑን የሚያጎላ ትክክለኛ፣ ሰው ተኮር እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ዘገባን ለማበረታታት ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

በመርሐ ግብሩ በፍልሰት፣ በግዳጅ መፈናቀል፣ በሠራተኞች እንቅስቃሴ፣ በሰዎች ነፃ ዝውውር፣ በምቹ የሥራ ዕድል፣ እና በቀጣናዊ ትስስር ዙሪያ የላቀ የጋዜጠኝነትና የዲጂታል ታሪክ አተራረክ ሥራዎችን ያቀረቡ ባለሙያዎች ይሸለማሉ።

መድረኩን በይፋ የከፈቱት የኡጋንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቢናህ ናባንጃ ባደረጉት ንግግር፤ የኢጋድ ቀጣና በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ ከሚስተዋልባቸው ኮሪደሮች አንዱ ነው።

ዜጎች ለሥራ፣ ለትምህርት፣ ለንግድ እና ለተሻለ ኑሮ ድንበር አቋርጠው እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመዋል።

አርብቶ አደሮች ውሃና ግጦሽ ፍለጋ ሲንቀሳቀሱ ሌሎች ደግሞ በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት እንደሚፈናቀሉ አብራርተዋል።

ስለሆነም የሰዎች የተረጋጋ እንቅስቃሴ ሰብዓዊ ወይም የደህንነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ማህበራዊ ለውጥ እና ቀጣናዊ ትስስር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ደህንነቱ የተጠበቀ እና ሥርዓት ያለው የሰዎች እንቅስቃሴ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን፣ የክህሎት ልማትን፣ ሥራ ፈጠራን እና ቀጣናዊ ትስስርን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

በአንጻሩ ሕገወጥ እና አደገኛ የሰዎች እንቅስቃሴ እንደ ሴቶች እና ወጣቶች ያሉ ተጋላጭ ክፍሎችን ለብዝበዛ፣ ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ለመብት ጥሰት እንደሚያጋልጥ ጠቅሰው፤ ፍልሰትን ወደ ዕድል፣ ብልፅግና እና ሰብዓዊ ክብር መቀየር የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል።

ፍልሰት ብዙውን ጊዜ በቀውስ እና በአለመረጋጋት መነጽር ብቻ እንደሚታይ ተናግረው መገናኛ ብዙሃን የጽናት፣ የፈጠራ፣ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ፣ የሰላማዊ አብሮነት እና የቀጣናዊ ትብብር ታሪኮችንም ማጋራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ኃላፊነት የሚሰማው ጋዜጠኝነት የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመሞገት፣ መጤ ጠልነት ለመከላከል፣ ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ሕዝባዊ ውይይትን ለማበረታታት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የስደተኞችን እና የተቀባይ ማህበረሰቦችን ድምጽ የማጉላት ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የ2026ቱ የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት ለጋዜጠኝነት ልህቀት እውቅና ከመስጠት ባለፈ በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብ፣ ተጠያቂነት ያለው አስተዳደር እና አካታች ቀጣናዊ ትስስርን ለመገንባት የሚደረግ ኢንቨስትመንት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም