ቀጥታ፡

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ወደ ትርፍ አምራችነት የቀየራቸው የወልመራ አርሶ አደሮች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2019(ኢዜአ)፦  በኋላቀር የበሬ እርሻ፣ በዓመት አንዴ በሚዘንብ ዝናብ እና በተቆራረጡ ማሳዎች ላይ ተመስርቶ የቆየው የኢትዮጵያ ግብርና፣ አርሶ አደሩን ከችግር፣ ሀገሪቱንም ከእርዳታ ጠባቂነት ማውጣት ሳይችል ቆይቷል።

ይሁን እንጂ የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥና የተረጂነትን ታሪክ ለመቀየር ባስቀመጠው አዲስ የልማት አቅጣጫ፣ ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። 

የመደመር እሳቤ ሀገር በቀል ዕውቀትንና የተፈጥሮ ሀብትን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ ከኩታገጠም እርሻ እና ከግብርና ሜካናይዜሽን ጋር በማቀናጀት የማህበረሰቡን የሥራ ባህል ቀይሮታል። 

በዚህም ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት ባለፈ፣ ስንዴን ወደ ውጭ መላክ ብሎም አርሶ አደሩን ወደ ትርፍ አምራችነት ያሸጋገረ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው። 

በጅማ ከተማ የሚከበረውን 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የመገናኛ ብዙሃን የመስክ ጉብኝት በክልሉ የሚገኙ የልማት ጸጋዎችን እየቃኘ ይገኛል። 

የጉብኝቱ አንዱ አካል የሆነው በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን የሚገኘው የወልመራ ወረዳ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ አስደናቂ የልማት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በወረዳው ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ተሾመ ጢቆ "ከአራት ዓመታት በፊት ይህ አካባቢ የአዋሽ ወንዝ የሚያስከትለውን ጎርፍ የምንሸሽበት እንጂ ስንዴ ይበቅልበታል ተብሎ የሚታሰብ አልነበረም" ይላሉ።  

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ህዝቡ የስንዴ ልማትን እንደማያውቅ ጠቅሰው በግብርና ባለሙያዎች ያላለሰለሰ ጥረት የጀመሩት የበጋ መስኖ ስንዴ ዛሬ ታሪካቸውን ቀይሯል፡፡  

የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውኃን በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜ ስንዴ ማምረት ማቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡  

"አሁን መሬታችን ፆም አድሮ አያውቅም፤ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ተላቅቀን ሕይወታችን ተቀይሯል " በማለት የኩታገጠም እርሻና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያመጣውን ለውጥ ይመሰክራሉ።

ወጣት ገዙ ጫላ በበኩሉ፣ በአካባቢያቸው የሚገኙ ከ500 በላይ አርሶ አደሮች በክላስተር ተደራጅተው ስንዴ በስፋት እያመረቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ በአርሶ አደሮቹ ጓዳ የፈጠረው መትረፍረፍ በአርሶ አደር ደንደና ጉዲሳ ሕይወት ውስጥ በግልጽ መታየቱን ነው የገለጹት፡፡

ይህም የአርሶ አደሮችን የኑሮ ደረጃ በተጨባጨ መለወጡን ጠቅሰዋል፡፡  

"ዛሬ ልጆቼን ያለ ችግር እያስተማርኩ፣ የአፈር ማዳበሪያ በቀላሉ እየገዛሁ፣ ከፍጆታዬ ተርፎኝም በባንክ ተጨማሪ ሂሳብ ከፍቼ መቆጠብ ጀምሬያለሁ" በማለትም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

በበኩታ ገጠም መደራጀታቸው ሰብላቸውን በጋራ ለመጠበቅና ለመንከባከብ ከማስቻሉም በላይ፣ ምርቱን በሕብረት በመሰብሰባቸው ቀደም ሲል ያጋጥም የነበረውን የምርት ብክነት በእጅጉ እንደቀነሰላቸው አርሶ አደር ደንደና አብራርተዋል። 

ለዚህ ሁሉ ስኬት ደግሞ መንግሥት የሚያደርግላቸው ያልተቋረጠ ድጋፍ ትልቅ ድርሻ እንዳለው የጠቆሙት ደግሞ አርሶ አደር አርሶ አደር ተሾመ ጢቆ ናቸው፡፡ 

የወልመራ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ሂርጳ እንደገለጹት፣ በወረዳው ብቻ ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ ይገኛል ብለዋል። 

እንደ ሌማት ትሩፋት እና የአትክልትና ፍራፍሬ ክላስተር ያሉ ኢኒሼቲቮች ታክለውበት፣ የወልመራ አርሶ አደሮች ለሀገር የሚተርፍ ምርት የማምረት ራዕይን በተግባር እያረጋገጡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም