ቀጥታ፡

በነፃ ንግድ ቀጠናዎች የባለሃብቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የተቀናጀ የፋይናንስ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

ድሬደዋ፤ ህዳር 10/2019 (ኢዜአ)፦ በነፃ ንግድ ቀጠናዎች የባለሃብቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የተቀናጀ የፋይናንስ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።

ኮርፖሬሽኑ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር በመተባበር "የላቀ የፋይናንስ አገልግሎት ለነፃ ንግድ ቀጠናዎች ተወዳዳሪነት" በሚል መሪ ሃሳብ በድሬዳዋ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ከተማ በወቅቱ፤ ኮርፖሬሽኑ በገነባቸው 14 ስትራቴጂካዊ ፓርኮች ውስጥ 300 የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ወደ ስራ ገብተዋል። 

እነዚህ ፓርኮች በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝትና ተኪ ምርቶችን በማምረት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የምክክር መድረኩ የፋይናንስ ተቋማት አመራሮችና ባለሃብቶች ተናበው እንዲሰሩና ዘላቂ የብድር ምቹነት እንዲፈጠር የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም አንስተዋል።

በመድረኩ በባለሃብቶችና በፋይናንስ ተቋማት መካከል የተፈጠረው የጋራ መግባባትና የተናበበ ቅንጅት፤ በፓርኮቹ የሚሰሩ ባለሃብቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በማሳደግ የኢትዮጵያን ከፍታና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶችን ከዳር ለማድረስ ወሳኝ መደላድል ይፈጥራል ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አደም፤ ቀጠናው ለጅቡቲ ወደብና ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ባለው ስትራቴጂካዊ ቅርበት እና በተሟሉ መሠረተ ልማቶች ባለሃብቶችን እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ለቀጠናው ውጤታማነትና መስፋፋት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ መልዕክተ ሳህሉ በበኩላቸው፤ ባለሃብቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና አሸናፊ እንዲሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ዘመናዊ ዲጂታል ድጋፍና ብድርን ይበልጥ ማቀናጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ የፋይናንስ ተቋማት አመራሮችና ባለሃብቶችም በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የአገርን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ተቀናጅቶ መስራትና መሰል የምክክር መድረኮችን ማጠናከር እንደሚገባ አስታውቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም