ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት አቅሟን በማሳደግ ለአፍሪካ የአቅርቦት ሰንሰለት ወሳኝ አቅም እየገነባች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት አቅሟን በማሳደግ ለአፍሪካ የአቅርቦት ሰንሰለት ወሳኝ አቅም እየገነባች ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2019(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት አቅሟን በማሳደግ ለአፍሪካ የአቅርቦት ሰንሰለት ወሳኝ አቅም እየገነባች መሆኑን የአፍሪካ ሀገራት የፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ባለሙያዎች ገለጹ።
19ኛው ዓለም አቀፍ የህክምና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሔደ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የጤና ፖሊሲን በማሻሻል ፣ የመድኃኒት አቅርቦቱን ከጥገኝነት ለማላቀቅ እና ጠንካራ የጤና ሥርዓት በመገንባት ረገድ ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል።
በጥቂት ዓመታት ብቻ የሀገር ውስጥ የመድሃኒት አቅርቦትን ከ8 በመቶ ወደ 46 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል።
አስተያየታቸወን ለኢዜአ የሰጡ የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የፋርማሲዩቲካል ባለሙያዎች ኢትዮጰያ በጤናው ዘርፍ ፈጣን እድገት እያስመዘገበች ትገኛለች።
በተለይም የመድሃኒት አቅርቦትን በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን እየተደረገ ያለው ጥረት በእጅጉ የሚበረታታና የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚምባብዌ የመጡት ፋርማሲስት ትራቮር ማቡጉ፣ ኢትዮጵያ በመድኃኒት ምርት የምታሳየው እድገት ከሀገሪቱ ውስጣዊ ፍላጎት ባለፈ ለአፍሪካ አህጉር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን የሕዝብ ቁጥርና የገበያ አቅም በመጠቀም የመድኃኒት ምርቷን ማስፋፋትና ምርቶቿን ወደ ጎረቤት ሀገራትና መላው አፍሪካ ማድረስ እንደሚገባት አመልክተዋል።
በዚህ ረገድ በአፍሪካ አምራች ሀገራት መካከል የጋራ ግዥ ሥርዓትን ማጠናከር የአህጉሪቱን የመድኃኒት ምርትና ተደራሽነት ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሌሴቶ ጤና ሚኒስቴር የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር ዳይሬክተር ቱሜሎ ሞቴቤ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በመድኃኒት ምርት ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ዕድገት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮና መነሳሳት ፈጥሯል ብለዋል።
ሌሴቶ በአሁኑ ወቅት ውስን የመድኃኒት ማምረቻ አቅም እንዳላት ጠቁመው፣ ከኢትዮጵያ ተሞክሮ በመቅሰም የሀገራቸውን የመድኃኒት ኢንዱስትሪ ማሳደግ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
የናይጄሪያ ጤና ሚኒስቴር ባልደረባ ባሺር ዩሱፍ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዘርፍ እያከናወነች ያለው ሥራ የሚደነቅና ለሌሎች አፍሪካውያን ሀገራት አርዓያ የሚሆን ነው ብለዋል።
በተለይም በዘርፉ የሚሠሩ ባለሙያዎች ብቃት፣ የሠራተኞች ቁርጠኝነትና የአቅርቦት ሥርዓቱ የሥራ አቅም ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር የሚመጣጠን መሆኑን ከጉብኝታቸው መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
አክለውም የዘርፉን የሰው ኃይል ብቃት ማሳደግ ለመድኃኒት ምርትና አቅርቦት ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።