አዲስ አበባ የቱሪስቶች ዋነኛ መዳረሻና መቆያ ማድረግ የሚያሽችሉ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ የቱሪስቶች ዋነኛ መዳረሻና መቆያ ማድረግ የሚያሽችሉ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2019(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ የጎብኚዎች መሸጋገሪያ ብቻ ሳትሆን ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻና መቆያ ማድረግ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር ገለጹ።
ከአንድ መቶ በላይ አባላትን የያዘው "የውቢቷ አዲስ አበባ የቱሪስት አስጎብኚዎች ማህበር" በይፋ ተመስርቷል፡፡
አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር በዚሁ ወቅት፤ በከተማዋ የተገነቡት የኮሪደርና የወንዞች ዳርቻ ልማቶች እንዲሁም አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች አዲስ አበባን የዓለም ተመራጭ የቱሪዝምና የኮንፍረንስ ማዕከል ለማድረግ ትልቅ አቅም መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
የጎብኚዎችን ልብ ለመማረክና ቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም ከመሠረተ ልማትና ከቅርሶች ባለፈ የአገልግሎት ጥራትና የአስጎብኚዎች ሙያዊ ብቃት ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አዲሱ ማኅበር አባላቱን በሥነ-ምግባር፣ በሙያዊ ክህሎትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማጎልበት፤ ከተለመዱት የጉብኝት ቦታዎች ባሻገር የምግብ፣ የኪነ-ጥበብና የኮንፍረንስ ቱሪዝም ዘርፎችን በማስፋፋት የከተማዋን የቱሪዝም አማራጮች እንዲያሰፋ አስገንዝበዋል፡፡
የውቢቷ አዲስ አበባ የቱሪስት አስጎብኚዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ሆሎፋ በበኩላቸው፤ ማህበሩ ከፌዴራል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በነሐሴ 2018 ዓ.ም ህጋዊ እውቅና አግኝቶ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።
ማህበሩ ከመቶ በላይ ልምድ ያላቸው የቱሪዝምና የሆቴል ባለሙያዎችን በማቀፍ፣ የከተማዋን ታሪካዊ ለውጥና ውበት በተደራጀ አግባብ ለዓለም ለማስተዋወቅ መመስረቱን ተናግረዋል።