አምስት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ከለንደን ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ - ኢዜአ አማርኛ
አምስት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ከለንደን ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2019 (ኢዜአ)፦ አምስት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ከለንደን ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል።
በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፣ በአሜሪካው የቶሌዶ ሙዚየም (TMA) እና በግል ቅርስ ሰብሳቢው ሮበርት (ቦብ) ማካርቲ ስብስብ መካከል በተመሠረተው የረጅም ጊዜ የትብብር ማዕቀፍ መሰረት ቅርሶቹ መመለሳቸው ተገልጿል።
የመጀመሪያ ዙር የሆነው የቅርስ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ትናንት ለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከናውኗል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ በታላቋ ብሪታንያና ሰሜን አየርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ክቡር ብሩክ መኮንን፣ የያንግ ላይቭስ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር አሉላ ፓንክረስት እንዲሁም በቶሌዶ ሙዚየም የስትራቴጂክ ጉዳዮች ረዳት ዳይሬክተር ዶክተር ሶፊ ኦንግ የርክክብ ሰነዱን በመፈራረም ዝውውሩን አረጋግጠዋል።
ወደ ሀገር ቤት የተመለሱት ቅርሶች በሥዕሎችና በጌጣጌጥ ያሸበረቁ ሁለት የ15ኛው ክፍለ ዘመን የብራና ጽሑፎች እና ከ18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ የተሠሩ ጽሑፍ የተቀረጸባቸው ሦስት የብረት መስቀሎች ናቸው።
የቶሌዶ ሙዚየም ባካሄደው የመጀመሪያ ዙር የምንጭና ባለቤትነት (Provenance) ጥናት፣ ሁለቱ የብራና ጽሑፎች እ.ኤ.አ. ከ1970 በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደነበሩ በሰነድ በመረጋገጡ በዘረፋ የወጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
ቅርሶቹ ወደ ኢትዮጵያ ከመመለሳቸው በፊትም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ባለሙያዎች ትብብር ወደ ዲጂታል ቅጂ እንዲለወጡ በመደረጉ፣ ለወደፊት አካዳሚያዊ ጥናትና ምርምር ተደራሽ ሆነው እንዲቀጥሉ ተመቻችቷል።
በሦስቱ መስቀሎች ላይ ደግሞ ተጨማሪ ምርምር በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የሚካሄድ ይሆናል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ብሩክ መኮንን፣ ርክክቡ የኢትዮጵያን ባህላዊ ቅርስ ከመጠበቅ ባለፈ ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ዶክተር አሉላ ፓንክረስት እና ዶክተር ሶፊ ኦንግ በበኩላቸው፣ ይህ ስምምነት ቅርሶችን ከመመለስ ባሻገር በምርምር፣ በአያያዝና በባለቤትነት ጉዳዮች ዙሪያ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል ዘላቂ አሠራርን የሚዘረጋ መሆኑን አስገንዝበዋል።
እ.አ.አ በሴፕቴምበር 2026 በተፈረመው የረጅም ጊዜ ስምምነት መሠረት፣ በሚቀጥሉት ዓመታትም በማካርቲ ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ተጨማሪ ቅርሶች በቶሌዶ ሙዚየም በኩል ጥናት እየተደረገባቸው ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ።
ተመላሽ የሆኑት አምስቱ ቅርሶች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም እ.ኤ.አ. በዲሴምበር ወር 2026 ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ እያዘጋጀው ባለው አዲስ የተመለሱ ቅርሶች ኤግዚቢሽን ላይ ለዕይታ ይቀርባሉ።
በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ እ.ኤ.አ. በ2024 ወደ ሀገር የተመለሰው የመቅደላ ጋሻ በማዕከላዊነት እንደሚቀርብም ተመልክቷል።