በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ከ2 ሺህ 470 ኪሎ ሜትር በላይ መስመሮች ግንባታ እና የማስፋፊያ ስራ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ከ2 ሺህ 470 ኪሎ ሜትር በላይ መስመሮች ግንባታ እና የማስፋፊያ ስራ ተከናውኗል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት 2 ሺህ 472 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመሮችን የመልሶ ግንባታ፣ የማሻሻያና የማስፋፊያ ሥራ ማከናወኑን ገለጸ።
በነባር መስመሮች ላይ በተከናወነው የመልሶ ግንባታና የማሻሻያ ሥራ 749 ኪሎ ሜትር መካከለኛ መስመር እና 82 ኪሎ ሜትር ዝቅተኛ መስመር፣ በድምሩ 831 ኪሎ ሜትር ሥራ ተሰርቷል።
በተጨማሪም ከአቅማቸው በላይ በጭነት ምክንያት የአገልግሎት መቆራረጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ 481 ትራንስፎርመሮች በከፍተኛ አቅም ባላቸው ትራንስፎርመሮች ተተክተዋል።
እንዲሁም 411 ተጨማሪ ትራንስፎርመሮች በተለያዩ አካባቢዎች ተከላ ተደርጎላቸዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋንን ለማስፋፋት በተከናወነው ሥራ ደግሞ 978 ኪሎ ሜትር መካከለኛ መስመር እና 662 ኪሎ ሜትር ዝቅተኛ መስመር፣ በድምሩ 1 ሺህ 641 ኪሎ ሜትር አዲስ መስመር መዘርጋቱን ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው።
በእነዚህ የማስፋፊያ ሥራዎች 1 ሺህ 744 ትራንስፎርመሮችም ተከላ ተደርጎላቸዋል።
እነዚህ ሥራዎች በተቋሙ የውስጥ ፋይናንስ ብቻ መከናወናቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የነባር መስመሮችን ጥራትና አቅም ለማሻሻል፣ የኤሌክትሪክ ሽፋንን ለማስፋፋት እና የአገልግሎት ተደራሽነትንና ቀጣይነትን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አመልክቷል።
የመስመሮች መልሶ ግንባታና ማሻሻያ፣ የትራንስፎርመሮች አቅም ማሳደግ እና አዳዲስ መስመሮችን መዘርጋት የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማጠናከር፣ የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻልና የኢንዱስትሪ፣ የንግድ፣ የግብርና እና የማኅበራዊ አገልግሎቶች ዕድገትን ለመደገፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን፣ የኔትወርክ አቅምንና የአቅርቦት ቀጣይነትን ለማጠናከር የጀመራቸውን የመልሶ ግንባታ፣ የማሻሻያና የማስፋፊያ ሥራዎች በቀጣይነት እንደሚያከናውን አስታውቋል።