ቀጥታ፡

በከተማ ግብርና መሰማረታችን የተሻለ ገቢ እንድናገኝ አስችሎናል - ወጣቶች

ሐረር፤ ህዳር 10/2019 (ኢዜአ)፦ በከተማ ግብርና፣ በከብት ማድለብና በንብ ማነብ ሥራ መሰማራታቸው የገቢ አቅማቸውን እንዳሳደገላቸው የሐረሪ ክልል ወጣቶች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የከተማ ግብርና በዋናነት ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ሆኗል። 

በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙት የሌማት ትሩፋት እና መሰል የግብርና ልማት መርሃ ግብሮች፣ በከተማ አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች በአነስተኛ ቦታዎች ላይ ውጤታማ የግብርና ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።

በሐረሪ ክልልም የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ወጣቶች በማኅበር ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ሰፊ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል። 

በዚህም መሠረት ለወጣቶቹ የመስሪያ ቦታዎችን የማመቻቸት፣ የመነሻ ካፒታል አቅርቦት፣ እንዲሁም በዘመናዊ የከብት ማድለብና የንብ ማነብ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮረ የክህሎት ሥልጠና የመስጠት ሥራዎች ተከናውነዋል።

ይህ እንቅስቃሴም የወጣቶችን የገቢ አቅም ከማሳደጉም በላይ፣ በከተማዋ የሚታየውን የምርቶች አቅርቦት በማሻሻል የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ ከከብት ማድለብና ወደ ውጪ አገራት በመላክ ውጤታማ ከሆኑ  የሐረር  ከተማ ነዋሪዎች ውስጥ ወጣት ኦሳማ ኢሳቅ  ይገኝበታል።

ወጣቱ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ በከተማ ግብርና የከብት ማድለብ ስራውን ከቤተሰብ እንደወረሰውና እያዘመነው እዚህ ደረጃ ደርሷል።

በየሶስት ወራት ከብት እያደለበ በዓመት አራት ጊዜ ወደ ውጭ ሀገራት እስከ 150 የሚደርሱ የደለቡ በሬዎችን በመላክ የውጪ ምንዛሬ እያስገኘ ስለመሆኑም አትቷል።

"በእንስሳት ሃብት ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢትሆንም አገሪቷ የሚፈለገውን ገቢ  ሳታገኝ ቀርታለች” የሚለው ወጣቱ፤  በዚህ ላይ መስራት እንደሚገባና እሱም ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል።

በዱባይ ለስምንት ዓመታት በስደት የኖረውና ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሶ በንብ ማነብ ስራ የተሰማራው  ወጣት ነስረዲን አህመድ በበኩሉ፤ በሁለት ቀፎ የጀመረው ስራ በአሁኑ ወቅት ወደ 300 በማሳደግ በዓመት እስከ 2ሺህ ኪሎ ግራም ማር እንደሚያርት ተናግሯል።

ከማር ምርት በተጨማሪ ሰምና ሌሎች ምርቶችንም በማምረት ወደ ገበያ የማቅረብ ሰራ እያከናወነ ስለመሆኑ ይጠቅሳል።

“በአሁኑ ወቅትም ምርቱን ወደ ድሬዳዋ፣ ባቢሌ ከተሞችና ሌሎች ከተሞች በማስፋፋት እየሰራሁና ለወጣቶችም የስራ እድል እየፈጠርኩ ነው” የሚለው ወጣት ነስረዲን፤ ወጣቶች ከስደት ይልቅ በአገር ሰርተው መለወጥን ከእኔ መማር ይገባቸዋል ሲል ምክሩን ለግሷል።

በሐረሪ ክልል ግብርና ልማት ቢሮ የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ዳይሪክተር ናኦል አብዱማሊክ እንዳሉት፤ በመደመር መንግስት እይታ ትኩረት የተሰጠው የከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት ስራዎች  በክልሉ ውጤት እያስገኘ ነው።

በተለይ አርሶ አደሩን፣ ባለሃብቱንና ወጣቶችን በማሳተፍ የሚከናወኑት ተግባራት በዘርፉ ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት እያስቻሉ ነው ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም