ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትና የሰው ኃይል ግንባታ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን ውጤታማ ተግባር አከናውናለች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2019(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ባለፉት አሥር ዓመታት በተገበረችው ብሔራዊ የቀዶ ሕክምና ዕቅድ አማካኝነት የአገልግሎቱን ተደራሽነትና የባለሙያዎችን ቁጥር በማሳደግ ረገድ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን ውጤታማ ተግባር ማከናወኗን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉቀን አርጋው ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን የገለጹት ዛሬ በአዲስ አበባ በተጀመረው 4ኛው የፓን-አፍሪካ የቀዶ ሕክምና ፎረም የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ነው።

ፎረሙ “ለአፍሪካ የቀዶ ሕክምና ጤና እንክብካቤ አህጉራዊ የድርጊት ማዕቀፍ” በሚል መሪ ሐሳብ ከኅዳር 10 እስከ 12 ቀን 2019 ዓ.ም ለሦስት ቀናት ይካሄዳል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ዶክተር ሙሉቀን አርጋው፣ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶችን ወደ ማኅበረሰቡ በማቅረብ ረገድ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ውጤት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተምሳሌትነት የሚወሰድ ልምድ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚሁ መሠረት መሠረታዊ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማት ድርሻ ከነበረበት 44 በመቶ ወደ 78 በመቶ ማደጉን ጠቅሰዋል።

የቀዶ ሕክምና፣ የማደንዘዣ (አንስቴዥያ) እና የማህፀን ባለሙያዎች ጥምርታ ለ100 ሺህ ሕዝብ ከ0 ነጥብ 35 ወደ 5 ነጥብ 9 ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ታካሚዎች ለቀዶ ሕክምና ወረፋ የሚጠብቁበት አማካይ ጊዜ በአሥር ቀናት መቀነሱን እና የቀዶ ሕክምና መረጃዎችን ቀድሞ በነበረው ብሔራዊ የጤና መረጃ ሥርዓት ውስጥ በማካተት ክትትል ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

በቀጣይም ከ2026 እስከ 2030 (እ.ኤ.አ) በሚተገበረው አዲሱ ብሔራዊ ዕቅድ የተመዘገቡትን ውጤቶች ይበልጥ በማጠናከር የአገልግሎት ጥራትንና የባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ፣ እንዲሁም የግል ጤና ተቋማትን በመረጃ ሥርዓቱ ለማካተት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም