በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት ሊባክን የነበረን የመንግስት ሀብትና ንብረት ማዳን ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት ሊባክን የነበረን የመንግስት ሀብትና ንብረት ማዳን ተችሏል
ወላይታ ሶዶ፤ ኅዳር 10/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት ሊባክን የነበረን የመንግስት ሀብትና ንብረት ለማዳን መቻሉን የክልሉ ሥነ-ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አለማየሁ ባውዲ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2019 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ዘርፍ ብዙ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት ለኮሚሽኑ በአካል፣ በስልክ፣ በቴሌግራም እና በሌሎች አማራጮች የቀረቡ ጥቆማዎችን በአግባቡ ከመመዝገብ ባለፈ የመረጃ አስተዳደር፣ አደረጃጀትና አሠራርን የማዘመን ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
በፈጣን ሙስናን የመከላከል ሥራም በሩብ ዓመቱ ለኮሚሸኑ ለቀረቡ 25 ጥቆማዎች ምላሽ ለመስጠት ተችሏል ብለዋል።
በዚህም ሊባክን የነበረን የመንግስት ሀብትና ንብረት ለማዳን ተችሏል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በሩብ ዓመቱ ተመዝብሮ የነበረን የመንግሥት መሬት ለማስመለስ በተደረገ ክትትል 30 ሄክታር የገጠር ኢንቨስትመንት ይዞታን ለማስመለስ ተችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም 1ሺህ 898 ካሬ ሜትር የከተማ መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን ኮሚሽነሩ ገልጸው፣ ሊመዘበር የነበረ 585 ሺህ 700 ብር በላይ የመንግስት ሀብትንም ለማዳን መቻሉን አመልክተዋል።
በህገወጥ መንገድ ወደ ግለሰቦች ሊተላለፍ የነበረን 2 የመንግስት ቤት ለማዳን እንደተቻለም ጠቁመዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ሳሙኤል በበኩላቸው እንዳሉት፣ በከተማው ሙስናን ለመከላከል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው።
በተለይ የሙስና ተግባር በህዝብና በሀገር ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የግንዛቤ ማስበጫ ትምህርት መሰጠቱን አንስተዋል።
በሩብ ዓመቱ ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ 115 መዝገቦችን መመርመር የተቻለ ሲሆን የተጋነኑ እና ተገቢ ያልሆኑ የካሳ ክፍያዎች መልሰው እንዲከለሱ መደረጉን አቶ ደስታ ተናግረዋል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በከተማው የኦዲት ጉድለት ምርመራ መደረጉንና በዚህም ከ256 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ለማስመለስ መቻሉንም አመልክተዋል።
ከነጋዴዎች ጋር ባልተገባ ጥቅም ተቆራኝተው የመንግስትን ሀብት ለምዝበራ የዳረጉ ዘጠኝ የገቢ መምሪያ ሠራተኞች ላይ የዲሲፕሊን ክስ በመመስረት በ3ቱ ላይ ወሳኔ መተላለፉንም ጠቁመዋል።
በሀሰተኛ ማስረጃ ማዘጋጀት ላይ የተሰማራ አንድ ሌላ ባለሙያም በእስራት እንዲቀጣ መደረጉን ገልጸዋል።