በኦሮሚያ ክልል ከ3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ከ3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2019(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በመኸር ወቅት ከተዘራው አጠቃላይ ሰብል ውስጥ ከ3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ ከሚሸፍን መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ለአርሶ አደሩ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን፣ የአፈር ማዳበሪያዎችንና ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን በስፋት አከናውኗል።
በተጨማሪም በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ሰፊ መሬት እንዲለማ መደረጉ የምርት መጠኑን ከማሳደጉም ባሻገር የመኸር ምርት ስብሰባውን በሜካናይዜሽን ለማከናወን ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
በአሁኑ ወቅት የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብና በተለያዩ የተባይ ምክንያት እንዳይባክን አርሶ አደሩን በማስተባበርና የማጨጃ ማሽነሪዎችን በስፋት በማሰማራት ምርቱን በፍጥነት የመሰብሰብ ሥራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ እንዳሻው ጀማነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ አጠቃላይ ከታረሰው መሬት ውስጥ 28 በመቶ የሚሆነው ሰብል ለስብሰባ ደርሷል።
እስካሁን በተደረገው ርብርብ ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ በተከናወነው የሰብል ስብሰባም 36 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት እንደ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ሩዝ፣ ቦሎቄ እና አተር ያሉ ዋና ዋና ሰብሎች እየተሰበሰቡ መሆኑን ጠቁመው፤ ሥራውን ፈጣን፣ ውጤታማና ከብክነት የጸዳ ለማድረግ የሰው ኃይልንና ቴክኖሎጂን በማቀናጀት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም የአርሶ አደሩ በደቦና በጅጊ እንዲሁም ተማሪዎችን ባሳተፈ የተቀናጀ ዘመቻ ከማስተባበር ባለፈ፣ 737 ኮምባይነሮችና 9 ሺህ 453 ተንቀሳቃሽ የሰብል መውቂያ ማሽኖች ወደ ሥራ መግባታቸውን አብራርተዋል።
የሰብል አሰባሰቡ እንዳይስተጓጎል ለኮምባይነሮች በቂ የነዳጅ አቅርቦት የማመቻቸት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፤ በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞኖች ደግሞ የአረም፣ የበሽታ ቁጥጥር እና የዝናብ ውሃ አጠቃቀም ሥራዎች በትኩረት እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
አቶ እንዳሻው አክለውም፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የምርት ጥራትን ለመጠበቅ ሰብሉ በትክክለኛው ወቅትና ዘዴ መሰብሰብ እንዳለበት አሳስበዋል።
የተሰበሰበው ምርትም ለረጅም ጊዜ እንዲቆይና እንዳይባክን በንጹህ፣ ደረቅና በቂ አየር በሚያስገቡ መጋዘኖች ውስጥ እንዲከማች ጥሪ አቅርበዋል።