ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፉ የፈጠረችው አቅም በ2030 በመስኩ ያስቀመጠችውን ግብ የሚያሳካ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፉ የፈጠረችው አቅም በ2030 በመስኩ ያስቀመጠችውን ግብ የሚያሳካ ነው
ዲላ፤ ህዳር 9/2019(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፉ የፈጠረችው አቅም በ2030 በመስኩ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
እንደ ሀገር ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ውስጥ ዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ሥራዎቹን ለማህበረሰቡ ተደራሽ እያደረገ መሆኑም ተመላክቷል።
በዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አዲሱ ፍሪጆ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት ዲጂታል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረግ ሥራን ከማቃለልና ከማቀላጠፍ ባለፈ የዘመናዊነት መገለጫ ነው።
በአሁኑ ወቅት ዓለም በዲጂታል ትግበራ ብዙ ርቀቶችን የተጓዘ በመሆኑ ኢትዮጵያ በዘርፉ ተወዳዳሪነትን ለማጠናከር እና ውዝፍ ሥራዎችን ለማካካስ በምታደርገው ጥረት ውጤታማ ተግባር እያከናወነች መሆኗን ነው የገለጹት።
በተለይ ከዲጂታል መታወቂያና አገልግሎት አሰጣጥ አንስቶ እስከ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የተገነባው የዲጂታል ሥርዓት በዘርፉ ትልቅ አቅም ፈጥሯል ነው ያሉት።
የተፈጠረው አቅምም በ2030 ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፉ ለመድረስ ያቀደችውን ግብ በላቀ ሁኔታ ለማሳካት የሚያስችላት ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያግዙትን ጨምሮ በመምህራንና ተማሪዎች የተገነቡ 10 የተለያዩ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረጉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ዲጂታል መሠረተ ልማትን በማስፋት እውቀት ተኮር ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ጥረት ተስፋ ሰጭ ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የኢ-ለርኒንግ ዳይሬክተር እንግዳ ኢሳያስ (ዶ/ር) ናቸው።
ይህም ለዜጎች ምርታማነት፣ ለአሰራር ቅልጥፍና እንዲሁም የሀብት ብክነትን በማስቀረት ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብት ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የመምህራንንና የተማሪዎችን የዲጂታል ክህሎት በማሳደግና የሳይበር ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይ በዘርፉ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግና የዲጂታል መሠረተ ልማት ማነቆዎችን ከመፍታት ባለፈ በዩኒቨርሲቲው የበይነ መረብ ትምህርት ባህልን እየገነባ መሆኑን አንስተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኢስቲሚ ማዕከል ተማሪ ገባል አብረሃም የተፈጥሮ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ቅድመ ጥቆማ የሚሰጥ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ለትግበራ ማብቃቱን ገልጿል።
ፈጠራውም የአየር ንብረት መረጃዎችን በማሰባሰብ በተለይ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭነትን ቀድሞ በመለየት ለአካባቢው መስተዳድርና ማህበረሰብ መረጃ የማድረስ ሥርዓትን የያዘ ነው ብሏል።
ይህም በመስክ ላይ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን አንስቶ የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠናና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ከዩኒቨርሲቲው ያገኘው ክህሎት ለፈጠራ ሥራው ትልቅ አቅም እንደሆነው ተናግሯል።