"ዱቡሻ ዎጋ" - የጋሞዎች የሰላምና የአብሮነት መሳሪያ - ኢዜአ አማርኛ
"ዱቡሻ ዎጋ" - የጋሞዎች የሰላምና የአብሮነት መሳሪያ
(በሳሙኤል አየነው - ኢዜአ አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ)
"ዱቡሻ ዎጋ" በጋሞ ማህበረሰብ ዘንድ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረና የዕርቅ ምንጭ የሆነ ባህላዊ የፍትህና የአስተዳደር ሥርዓት ነው። "ዱቡሻ" ማህበረሰቡ በአንድ ልብ ተሰብስቦ የሚመክርበት፣ ሕግ የሚደነገግበትና የተጣላን የሚያስታርቅበት አደባባይ ሲሆን "ዎጋ" ደግሞ የአደባባዩን ክብር የሚጠብቀውን ባህላዊ ሕግና ሥነ-ሥርዓት የሚያመላክት ነው።
የችግሮች መፍቻ፣ የሰላም መሠረትና የአንድነት መገንቢያ የሆነው "ዱቡሻ ዎጋ" የጋሞ ማህበረሰብ ባህላዊ የእርቅ ሥነ-ስርዓት በመሆኑም የፍትህ አደባባይ ነው ማለትም ይቻላል።
በዱቡሻ ዎጋ ማህበራዊ አለመግባባቶች፣ ግጭቶችና በደሎች በሽማግሌዎች ይፈታሉ። እርቅ የሚወርድበት፣ በደል የሚታረምበትና ተበዳይ የሚካስበት ሥርአት የሚከወንበት ስፍራም ነው። በዚህ የፍትህ አደባባይ ችግሩን በጊዜያዊነት ከመፍታት ይልቅ ግጭት ውስጥ በገቡ ሁለቱ ወገኖች መካከል የተበላሸውን ማኅበራዊ ግንኙነት ጭምር በመጠገን ወደ ቀድሞ አብሮነታቸው ለመመለስ በሚያስችል መልኩ ነው የሚፈታው።
የዱቡሻ የላቀ ጥበብ የሚታይበት አንዱም በዚህ ነው። የአንዱን ወገን ረቺነት ከማስቀደም ይልቅ ሁለቱም ወገኖች እውነትን ተቀብለው ከውስጥ የመነጨ እርቅ በማውረድ በሰላም እንዲኖሩ የሚያስችል መፍትሔ የሚሰጥበት ነው።
ዱቡሻ የጋሞ ማኅበረሰብ ሰላምና አንድነቱን ለማስጠበቅ የሚጠቀምበት ባህላዊ ሥርአት ሲሆን ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የጋራ ሀብቱም ነው ማለት ይቻላል።
ችግርን በምክክር፣ ግጭትን በእርቅ፣ ልዩነትን በመግባባት የሚፈታው ዱቡሻ ዎጋ፤ ከጋሞ ሕዝብ ባህላዊ እሴትነት ባለፈ ለሰው ልጅ የሰላምና የአብሮነት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ሀገር በቀል የጥበብ ሀብትም እንደሆነ ይነገራል። ዓላማውም በማኅበረሰቡ አባላት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ነው። በዚህ ሥርዓት ሽማግሌዎች የሁለቱንም ወገኖች ሐሳብ ተቀብለው ከዳመጡና እውነታውን ካጣሩ በኋላ በምክርና በሽምግልና ወደ መግባባት ያመጧቸዋል።
በዱቡሻ ዎጋ የእርቅ ሥነ ስርዓት "እርጥብ ሣር" እጅግ የላቀ ቦታና ትርጉም ይሰጠዋል። የሰላም መሳሪያ ነው ማለትም ይቻላል። የጋሞ አባቶች በእጃቸው እርጥብ ሣር ይዘው በተጋጪዎች መካከል ሲቆሙ የቱንም ያህል ለጥልና ለመገዳደል የተነሳሳ አካል ትጥቁን ፈትቶ ትልቅ ዋጋ ላለው ለሰላም ይገዛል።
ከዚህ የተነሳ በዱቡሻ ሥርአት የተፈጠሩት መካሪ አባቶች ብቻ ሳይሆኑ አባቶችን የሚሰማ ትውልድም እየተፈጠረ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ባህላዊ እሴት ቂምና በቀልን ከማህበረሰቡ ውስጥ በማስወገድ በምትኩ እርቅን፣ ሰላምና አብሮነትን እያሰፈነ ነው። በዚህም ዘመናዊውን የፍትህ ሥርዓት እያገዘ ያለ ተመራጭ የግጭት መፍቻም ነው ማለት ይቻላል።
ዱቡሻ የህዝብ ምክክር የሚካሄድበት፣ አዳዲስ ህጎች የሚደነገጉበትና ማህበራዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ታላቅ አደባባይ ነው። ግጭትና ቁርሾን በሰላማዊ መንገድ በማንም ላይ ቅሬታ ሳያድር መፍታት ጊዜና ጉልበትን ለልማት፣ ለትምህርትና ለጋራ ዕድገት ለማዋል ያስችላል። በዚህ ረገድ ዱቡሻ ካለው አስተዋጾ አንጻር የሰላም መሣሪያ ብቻ ሳይሆን የልማት መሠረትም ነው።
ዱቡሻ ዎጋ ከፍትህና ከሰላም መድረክነቱ ባለፈ ወጣቶች ስለ ማንነታቸው፣ ስለታሪካቸውና ስለማህበራዊ ሃላፊነታቸው ከታላላቅ ሽማግሌዎች የሚማሩበት ህያው ትምህርት ቤት እንደሆነም ይነገራል።
የጋሞን ማህበረሰብ አንድ አድርገው ያቆሙና ለዘመናት በቃል ሲወራረዱ የመጡ የህግና የሞራል እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት ነው። በዚህ ባህላዊ ሥርአት ለእውነትና ቅንነት ትልቅ ትኩረት ስለሚሰጥ በዱቡሻ ፊት ቆሞ መዋሸት እንደ ትልቅ ነውርና መንፈሳዊ መርገምት ወይም በጋሞዎች አጠራር "ጎሜ" ተደርጎ ይወሰዳል።
የዱቡሻ ዎጋ ሥርዓት በዛፎች ጥላ ሥር መካሄዱ በራሱ ልዩ ትርጉም አለው። ዛፍ ለሁሉም እኩል ጥላ እንደሚሰጥ ሁሉ በዚህ የፍትህ አደባባይ ፍትሕም ለሁሉም እኩል መሰጠት እንዳለበት የሚያሳይ ተምሳሌት ነው። በዚህም ምክንያት በዳይም ሆነ ተበዳይ ለእውነት ተገዢ ሆነው ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ያደርጋል። ይህም ለጋሞ ማህበረሰብ ሠላማዊና መረጋጋት መሠረት ሆኖ ቆይቷል።
ይህ ባህላዊ የእርቅ ሥርአት በሀገራችን ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ከመምጣቱ በፊት የነበረና ዛሬም ድረስ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ህዝብ በሰላም፣ በፍቅርና በመረዳዳት እንዲኖር ዘመን ተሻጋሪ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ወቅት ይህንን ታላቅ የባህል እሴት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማላቅ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህም ለዘላቂ ሰላምና አንድነት ካለው ፋይዳ ባለፈ የጋሞን ማህበረሰብ ታሪክና ማንነት በዓለም እንዲታወቅ፣ የባህል ቱሪዝም እንዲያድግና ለአካባቢው ኢኮኖሚ አዳዲስ ዕድል እንዲፈጠር ያግዛል።
ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው ይህ ባህላዊ ሥርዓት የህዝብን ሰላም፣ አብሮነትና መቻቻል በማጽናት ለማህበራዊ መረጋጋት የማይተካ አስተዋጾም እያበረከተ ይገኛል፡፡
በዓለም የተለያዩ ክፍሎች ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና ማኅበራዊ መከፋፈሎች በሚስተዋሉበት በዚህ ዘመን ማንንም ተጎጂ ሳያደርግ ችግሮችን በውይይትና በመግባባት የመፍታት ባህል ያለው ዋጋ ከፍተኛ ነው።
ለዚህም እንደ ዱቡሻ ያሉ ባህላዊ የእርቅ ሥርዓቶች በሰብአዊና ቁሳዊ ሀብቶች ላይ ኪሣራ ሳይደርስ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት ሁነኛ መፍትሄ ናቸው። በዱቡሻ ዎጋ የማይፈታ ማህበራዊ ችግር የለም። በሀቅ ላይ የተመሠረተ፣ ቂምና ቁርሾ የሌለውና ሁለቱንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግ በመሆኑ ተቀባይነቱ እያደገ መጥቷል።
የዱቡሻ ትልቁ መለያ ችግርን በግጭት ሳይሆን በምክክር፤ ልዩነትን በመከፋፈል ሳይሆን በመግባባት፤ ቂምን በበቀል ሳይሆን በይቅርታ መፍታት እንደሚቻል ማሳየቱ ነው።
የዱቡሻ ዎጋ የጋሞ ሕዝብ የትላንት ታሪክ ብቻ ሳይሆን የዛሬ ማኅበራዊ ሀብቱና የነገም ተስፋው ነው። ይህንን ባህላዊ የጥበብ ሀብት መጠበቅ፣ ማስተዋወቅና ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የማኅበረሰቡ፣ የምሁራን፣ የባህል ተቋማትና የመንግሥት የጋራ ኃላፊነት ነው። ሰላም!