ቀጥታ፡

ልማት የዛሬን ከተማ ብቻ ሳይሆን የነገን ታሪክም የሚጽፍ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ህዳር 10/2019(ኢዜአ) ፦ልማት የዛሬን ከተማ ብቻ የሚገነባ ሳይሆን የነገን ታሪክም የሚጽፍ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ አንዲት ከተማ የምትገነባው በመንገድና በሕንፃ ብቻ ሳይሆን ታሪኳን የሰሩና ለሀገር ውለታ የዋሉ ባለውለታዎቿን በክብር በማስቀጠል ጭምር መሆኑን አስገንዝበዋል።

በአደይ አበባ ስታዲየም አካባቢ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ስፖርት በማሳደግ ታላቅ አሻራ ያሳረፉትን ክቡር ይድነቃቸው ተሰማን የሚዘክር ሐውልት የተገነባውም ከዚሁ እሳቤ በመነሳት መሆኑን ጠቁመዋል።

"የአፍሪካ እግር ኳስ አባት" በመባል የሚታወቁት ይድነቃቸው ተሰማ ይህ ክብር የሚገባቸው መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ ለሀገርና ለትውልድ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ታላላቅ ሰዎችን መዘከር ታሪክን ከዛሬ ልማት ጋር በማስተሳሰር ለነገ ትውልድ ኩራትና መነሳሻ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ታሪክን እያከበረ፣ ማንነትን እያጠናከረና አሻራን ለትውልድ እያስተላለፈ የልማት ጉዞውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከንቲባዋ በመልዕክታቸው አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም