ኢትዮጵያና ስዊድን በአየር ንብረት ፋይናንስና በታዳሽ ኃይል ልማት ያላቸውን አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ስዊድን በአየር ንብረት ፋይናንስና በታዳሽ ኃይል ልማት ያላቸውን አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ስዊድን በአየር ንብረት ፋይናንስና በታዳሽ ኃይል ልማት ያላቸውን አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ አስታወቁ።
31ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርኪዬ አንታሊያ መካሄዱን ቀጥሏል።
ኢትዮጵያና ስዊድን ከጉባኤው ጎን ለጎን በአየር ንብረት ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከስዊድን የአየር ንብረትና አካባቢ ሚኒስትር ሮሚና ፑርሞክታሪ ጋር ባደረጉት ምክክር አድርገዋል።
ሚኒስትሩ በአየር ንብረት እርምጃ፣ በፋይናንስ አቅርቦት፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እንዲሁም በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፎች ያላቸውን አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ዘላቂ ልማትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ የዓለምን የሙቀት መጨመር በ1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ ወሰን ውስጥ ለመገደብ የተያዘውን ዓለም አቀፍ ግብ ለማሳካት የባለብዙ ወገን ትብብርና የማያቋርጥ ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን በጋራ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህም ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው የኮፕ 32 ዓለም አቀፍ ጉባኤ ስኬታማነት የሚያግዙ የትብብር መስኮችን በመለየት ስዊድን የበኩሏን ድጋፍ እንድታበረክትና በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ሚኒስትሮቹ መክረዋል።