ሀገር በአንድ ቀን ወይም በሌሊት የምትገነባ ሳይሆን በሂደትና በጋራ ጥረት የምትቀረጽ ናት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በአንድ ቀን ወይም በሌሊት የምትገነባ ሳይሆን በሂደትና በጋራ ጥረት የምትቀረጽ ናት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2019 (ኢዜአ)፦ሀገር በአንድ ቀን ወይም በሌሊት የምትገነባ ሳይሆን በሂደትና በጋራ ጥረት የምትቀረጽ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
በአዲስ አበባ 57 ሄክታር የሚሸፍን አዲስ የኮሪደር ልማት ሥራ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር )አዲስ አበባን ይበልጥ ውብና ማራኪ ለማድረግ ሰፊ የኮሪደር ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ የተመረቀው በአዲስ አበባ 57 ሄክታር የሚሸፍን አዲስ የኮሪደር ልማት ሥራ የዚሁ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአዲሱ የኮሪደር ልማት ውስጥ ሰፊ መንገዶች፣ የእግረኛ መንገዶች)፣ ፓርኪንግ፣ የኢቪ ቻርጂንግ ስቴሽኖች እና ለመዝናኛ የሚሆኑ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።
እንዲሁም የልጆች መጫወቻ ስፍራዎችና የብስክሌት መንገዶች መካተታቸው የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ እንደቀየረው ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት አዲስ አበባ ላይ ብቻ ሳይወሰን እንደ ሀዋሳ፣ አርባምንጭ፣ ጅማ፣ ሀረር፣ ጎንደር እና ነቀምት ባሉ የሀገሪቱ ከተሞችም በመስራት አበረታች የልማት ለውጦች መታየት መጀመራቸውንም ነው የገለጹት።
እነዚህ ከተሞች እየተገነቡባቸው ያሉት አቅጣጫዎች የህዝብን እንቅስቃሴ እና የንግድ ስራዎች በማቀላጠፍ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የተከናወኑት ስራዎች አበረታች ቢሆኑም፣ ገና ብዙ የቤት፣ የመንገድ፣ የፓርኪንግ እና የአገልግሎት መሰረታዊ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
ስኬቶችን በማድነቅ ብቻ ሳይወሰን፣ የቀሩትን ክፍተቶች ለመሙላት በትጋት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሀገር በአንድ ቀን ወይም በሌሊት የምትገነባ ሳይሆን በሂደትና በጋራ ጥረት የምትቀረጽ መሆኗን አስገንዝበዋል።
እኛ ራሳችን ተባብረን ካልሰራን ሌላ መጥቶ ሀገራችንን የሚሰራልን አካል ስለሌለ፣ በዚሁ መንፈስ ቀጥሎ ያሉትን ጅምሮች በድል ማጠናቀቅ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።