ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ዓለም አቀፉ የአካባቢ ተቋም (GEF) ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ዓለም አቀፉ የአካባቢ ተቋም (GEF) በአየር ንብረት ፋይናንስ እና በኮፕ 32 ዝግጅት ዙሪያ ያላቸውን አጋርነት የበለጠ ለማጎለበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርኪዬ አንታሊያ መካሄዱን ቀጥሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ተቋም (GEF) ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና ሊቀመንበር ዲዬጎ ሜሳ ፑዮ ጋር ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ የተካሄደው ለኮፕ 32 ዝግጅት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ማዕቀፍ ስር ነው።

የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የመጣጣም (Climate Adaptation) ሥራዎች እና በተለይም ለአየር ንብረት አደጋዎች በእጅጉ ተጋላጭ የሆኑ ታዳጊ አገራት አገራዊ ቅድሚያ ፍላጎቶቻቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር እንዲችሉ የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ ድጋፍ ለማሳለጥ በሚያስችሉ የትብብር አጋጣሚዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

ሁለቱ ወገኖች በተጨማሪም በነባር የገንዘብ ማሰባሰብ ዘዴዎች አማካኝነት ለአየር ንብረት ለውጥ የመጣጣም ድጋፍን ስለማጠናከር፣ ሕይወትንና መተዳደሪያን የሚጠብቁ በሀገራት የሚመሩ ፕሮግራሞችን ስለማሳደግ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራሞች በተገኙ ልምዶች በመነሳት የተራቆቱ መሬቶችን ወደ ቀድሞ ይዞታቸው የመመለስና የምግብና የውሃ ሥርዓቶችን የማጠናከር ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።

ኢትዮጵያ የኮፕ 32 ጉባኤን በአዲስ አበባ ለማስተናገድ ዝግጅቷን በምታጠናክርበት በዚህ ወቅት፣ ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ተቋም (GEF) ጋር ያለውን ቀጣይነት ያለው አጋርነትና ትብብር አስፈላጊነት ውይይቱ አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም