ቀጥታ፡

በጉራጌ ዞን የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ተማሪዎች ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉና ውጤታማ እንዲሆኑ እያገዘ ነው

ወልቂጤ፤ ሕዳር 9/2019 (ኢዜአ)፦ በጉራጌ ዞን የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ተማሪዎች ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉና ውጤታማ እንዲሆኑ እያገዘ መሆኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ በቅድመ መደበኛ እና በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል።

መርሀግብሩን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው በጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ የትምህርት ቤቶች መሻሻል ባለሙያ አቶ ለገሰ ጋዲሳ የትምህርት ውጤታማነተን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ከነዚህ ተግባራት መካከል የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ መርሀግብሩ በዞኑ በ47 የቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

ምገባው ከተጀመረ ወዲህ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉ ከማድረግ ባለፈ መጠነ ማቋረጥ እንዲቀንስ ማድረጉን ጠቁመው፣ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ በጊዜ እንዲገኙም አድርጓል ብለዋል።

ይህም የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ማድረጉን ያመለከቱት አቶ ለገሰ፣ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የምገባ መርሀ ግብሩን ለማጠናከር ይሰራል ብልዋል።

በወልቂጤ ሰላም በር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ገነት ሃይሌ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በትምህርት ቤቱ የተጀመረው የምገባ መርሀ ግብር ለትምህርት ጥራት መጠበቅ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

የምገባ መርሀግብሩን ተከትሎ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተረጋግተው እየተማሩና በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህም ውጤታማነታቸውን በማሳደግ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ አስተዋጾ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

የሰላም በር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ወይዘሮ እፀገነት ፍቃዱ 313 ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መርሀግብር ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል።

እንደ ርዕሰ መምህርቷ ገለጻ፣ መርሀግብሩ ተማሪዎች በጊዜ ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ፣ መጠነ ማቋረጥ እንዲቀንስና ውጤታማነታቸው እንዲጨምር እያገዘ ነው።

ልጃቸውን በወልቂጤ ሰላምበር ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት ወላጅ ወይዘሮ ፈለቀች ግርማ ፣ ልጃቸው የምገባ መርሀግብሩ ተጠቃሚ መሆኑ ለትምህርቱ የተሻለ ትኩረት እንዲሰጥ አድርጓል ብለዋል።

በአቅም ማነስ ምክንያት ለልጃቸው በየዕለቱ ምግብ ቋጥሮ ወደትምህርት ቤት ለመላክ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው፣ የምገባ መርሀግብሩ መጀመር ይህን ችግራቸውን እንደፈታላቸው ተናግረዋል። 

"የትምህርት ቤት ምገባ መርሀግብር ልጃቸው ያለሀሳብ ትምህርቷን ለመከታተል አስችሏታል" ያሉት ደግሞ በራስ ዘስላሴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጃቸውን የሚያስተምሩት ወላጅ ወይንሸት ከፍያለው ናቸው። 

ቀደም ሲል ልጃቸው ከትምህርት ቤት የምታረፍድበት እና የምትቀርበት አጋጣሚ እንደነበር አስታውሳ፣ በአሁኑ ወቅት ትምህርቷን በአግባቡ እየተከታተለች መሆኗን ተናግረዋል።

በመንግሥት፣ በማኅበረሰቡና በባለድርሻ አካላት ቅንጅት የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባለፈ የመማር ማስተማር ሂደቱን ይበልጥ ውጤታማ እያደረገ መሆኑም ይታወቃል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም