ቀጥታ፡

የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ዓለም አቀፉን የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃ በአግባቡ በመተግበር ለሪፖርት ጥራት ሊሰሩ ይገባል - የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2019(ኢዜአ)፦ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ዓለም አቀፉን የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃ (IFRS) በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ፣ ለፋይናንስ ሪፖርት ጥራት መረጋገጥ ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አሳሰበ።

ቦርዱ በፋይናንስ ሪፖርት ጥራት ዙሪያ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የቦርዱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለአነስተኛ ንግዶች፣ ለሴቶች፣ ለወጣቶችና ለአርሶ አደሮች እንዲሁም ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ በኢኮኖሚው ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። 

እነዚህ ባለድርሻ አካላት የተቋማቱን የፋይናንስ ጤናማነት ደረጃ የማወቅ መብት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን ትክክለኛ ቁመና የሚያሳየው ግልጽ በሆነ የፋይናንስ ደረጃዎች የተዘጋጀ ሪፖርት መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ተቋማቱ የሪፖርት ጥራትን የሚያስጠብቁ አሰራሮችን ሊተገብሩ እንደሚገባ አመልክተዋል። 

የፋይናንስ ሪፖርት ጥራት የተቋማቱ ውስጣዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚዎች፣ የባለአክሲዮኖች፣ የተቆጣጣሪ አካላትና የሕዝብ ጥቅም ጉዳይም ጭምር መሆኑን አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ዋና ዓላማ በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት፣ አሰራርና ጥራት ላይ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር በሰፊው በመምከር የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማመላከት መሆኑን ገልጸዋል። 

ቦርዱ ሪፖርት አቅራቢ ተቋማት ዓለም አቀፍ አሰራሮችን እንዲተገብሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ደረጃውን የማይተገብሩ አካላትን በተሰጠው ስልጣን መሰረት ተጠያቂ የማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አሳስበዋል።

የቦርዱ የፋይናንሻል ሪፖርቲንግ አማካሪ አቶ ፍቅሩ ፋንታሁን በበኩላቸው፤ ቦርዱ በ300 ተቋማት ላይ የፋይናንስ ሪፖርት ጥራት ግምገማ ማድረጉን ተናግረዋል። 

በግምገማውም በሪፖርት ውስጥ መካተት የሌለባቸውን መረጃዎች ማካተት እና መካተት ያለባቸውን ደግሞ አለማካተት ከተለዩ ዋና ዋና ችግሮች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተቋማቱ ሪፖርታቸውን ማዘጋጀት ያለባቸው ዓመቱ ሲያልቅ ለይስሙላ ብቻ ሳይሆን ጥራትን ታሳቢ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት የሰጡት አቶ ፍቅሩ፤ በሥራቸው ያሉ ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት ውጤታማ የፋይናንስ ሪፖርት ሥርዓት ሊገነቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የልዩ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የኮርፖሬት አገልግሎት ዋና ኦፊሰር አቶ ዘላለም መንገሻ እንደተናገሩት፤ በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች ላይ የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሊጠናከር ይገባል። 

ዘርፉ አዳዲስ ደረጃዎች በየጊዜው የሚወጡበት በመሆኑ፣ አዳዲስ ማሻሻያዎች ሲወጡ በመስኩ ላሉ አካላት በሰፊው የማስተዋወቅ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ የንስር ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የፋይናንስና ኢንቨስትመንት ማናጀር አቶ በረከት ሺፈራው፤ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ አሰራር ሥርዓቶች ዙሪያ ብቃትና ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት የሚከናወነው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም