የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከፍታ መልህቅ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከፍታ መልህቅ
መደመር የብሔራዊ ክብር ማገር፤ የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከፍታ መልህቅ!!
በመንግሥቱ ዘውዴ
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
ዲፕሎማሲ የሀገራትን ግንኙነት፣ ብሔራዊ ጥቅም፣ ክብርና የጂኦፖለቲካ ተጽዕኖን በውይይት፣ በድርድርና በስትራቴጂያዊ አጋርነት የማስጠበቂያ የመንግሥት ጥበብ ነው። የውጭ ግንኙነት ደግሞ በዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ሥርዓት ውስጥ የሀገርን ሉዓላዊነት፣ ደህንነትና የኢኮኖሚ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚከናወን ቀጣይ የስትራቴጂ ትግበራ ሲሆን፤ ስኬቱም በወዳጅነት ብዛት ሳይሆን በሀገራዊ ጥቅም መከበር ይለካል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ጉምቱ የተባሉ ጸሐፍት እንደሚገልጹት ዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት በመልካም ፍላጎት ብቻ የሚገነባ አይደለም።
ሐንስ ጄ.ሞርገንታው እ.አ.አ በ1948 ''Politics Among Nations: The Struggle for Power and Peace (1948) በሚል ባሳተሙት መጽሐፋቸው ባሰፈሩት መልዕክት፦ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ የሀገራት ባህሪ የሚወሰነው በሥልጣንና በብሔራዊ ጥቅም በተጋመደ መስተጋብር እንጂ በመልካም ፍላጎት ብቻ አይደለም። በዚህ የእውነታዊነት (Political Realism) ጽንሰ ሐሳብ መሰረት ዲፕሎማሲ የሀገርን ጥቅምና ኃይል በስልታዊ ድርድር የማስጠበቅ ጥበብ መሆኑን ልብ ይሏል።
የመደመር መንግሥት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም ወረትን በማሳደግ መግባባትና ትብብር፣ ብሔራዊ ጥቅምና ክብርን እንዲሁም ቅድሚያ ለጎረቤት የዲፕሎማሲ አካሄድን ይከተላል። ይህ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከውስጥ ሚነሳ የተደራሽነት አድማስን በማስፋት ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ የጂኦፖለቲካ ሁኔታን የሚመጥን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ስትራቴጂክ የወዳጅነት አቅሞችን እያጎለበተ ይገኛል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተጻፈው የመጀመሪያው መደመር መጽሐፍ ምዕራፍ አስራ ስድስት ላይ ''መደመር እና የውጭ ግንኙነት'' በሚል ርዕስ ሥር ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ሀገራችን ውዝፍ ሥራ ሳይሆን የዐቅም ክምችት ከፈጠረችባቸው መስኮች አንዱና ትልቁ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ መስክ ነው። ቀደም ባሉት መሪዎች እየተሠራ የመጣው መልካም የውጭ ግንኙነት ሥራ አሁን ለምንከተለው የውጭ ግንኙነት አካሄድ ትልቅ ወረት ሊሆነን የሚችል ነው። በአጠቃላይ በተከታታይ መንግሥታት ሲሠራ በነበረው መልካም የውጭ ግንኙነት ሥራ ምክንያት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ መልካም ስም አላት።
የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት ስኬት ከዓላማው በተሻገረ ተጨባጭ ውጤቱ ይመዘናል። የመደመር መንግሥት የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት ከውስጥ የሚነሳ፣ ለጎረቤት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ለአፍሪካ፣ ለዓለም አቀፍ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ትብብር መርህን ይከተላል።
የመደመር የውጭ ግንኙነት ፍልስፍናም የሰው ልጅን ተፈጥሮ በፉክክር ወይም በትብብር ከመበየን ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ሀገራትም ሆኑ መንግሥታት የግለሰቦች ስብስብ በመሆናቸው እነዚህ ሁለት የግንኙነት አማራጮች ይመለከቷቸዋል። ፉክክርን ወይም ትብብርን በሀገራትና በመንግሥታት ደረጃ የሚኖሩ ግንኙነቶች የሚገዙባቸው አማራጮች ናቸው።
የመደመር መንግሥት ቅድሚያ ለጎረቤት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም የኢኮኖሚ ትስስርን ከጋራ ዕድገትና ብልፅግና አቆራኝቶ የሚጓዝ ነው። በአፍሪካና በዓለም አቀፍ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የትብብር ሥርዓትም ብሔራዊ ጥቅምን ከሀገር ገናና ክብር አሰናሰለ ምቹ የትብብር ምኅዳር ፈጥሯል። ኢትዮጵያ የብሪክስ ቤተሰብ አባልነት፣ የዓለም አቀፍ ንግድ ድርጅት አባልነት በወሳኝ ምዕራፍ መድረሱ፣ በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ቁርጠኛ አቋም ሁነኛ አብነቶች ናቸው። ዛሬ ላይ አዲስ አበባ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብር የስበት ማዕከል ሆናለች።
የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ መድረክ ተሳትፎ
የኢትዮጵያ የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት የዕድገት ፍኖተ ካርታ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አስተማማኝ የኢኮኖሚ አቅም መገንባትን ያለመ ነው። በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማቶችም ለአካባቢ ተስማሚነት ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸው። የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የበጋ መስኖ ስንዴና የብዝኅ ዘርፍ የኃይል ሽግግር እመርታዊ የልማት ስልቶችም ኢትዮጵያን ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ቅነሳ ስምምነቶች ተገዥነት የገለጡ ተምሳሌቶች ናቸው።
የሰው ልጆች እና የቡና መገኛዋ ምድር ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ስም እየገነባች ይገኛል። ሶስት ሺህ ዓመታት የተሻገረ ገናና ጥንታዊ ሥልጣኔ ከዘመናዊ ከተሜነት በማሰናሰል በአስደማሚ የዕድገት ጉዞ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የዓለም ቀልብ ማረፊያ እየሆነች ነው። የአሸናፊዎች ምድር፣ የዲፕሎማሲ ማዕከልና የአፍሪካ የወደፊት የንጹሕ ኃይል መሪዋ ኢትዮጵያ በርካታ የመርህ ሀገር ይሏታል። ምክንያቱም ከቱርክዬዋ የሜዲትራኒያን ባሕር ጠረፍ ከተማ አንታሊያ የተረከበችውን የኮፕ-32 (COP-32) መድረክ በብቃት ለማስተናገድ እየተጋች ነውና።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንታሊያው የኮፕ-31 (COP-31) መድረክ በተጓዳኝ ከሀገራትና ዓለም አቀፍ መሪዎች ጋር ፍሬያማ የዲፕሎማሲ ውይይት አካሂደዋል። ከቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶጋን፣ ከባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ፣ ከቦትስዋና ፕሬዝዳንት ዱማ ጌዲዮን ቦኮ፣ ከኳታር አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል-ታኒ፣ ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ፣ ከኢራቅ ፕሬዝዳንት ኒዛር አሚዲ፣ ከኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆናስ ጋህር ስቶሬና ከፊንላንድ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ስቱብ ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን ማካሄዳቸው የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት የተፅዕኖ አድማስ በእጅጉ አጎልብቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ፍሬያማ የዲፕሎማሲ ምክክርም የኮፕ-32 (COP-32) መድረክ በብቃት ለማስተናገድ ከሚደረግ ዝግጅት ባሻገር የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና ክብር በእጅጉ ማጉላት ያስቻለ ነው። ይህም ከአንድ የጂኦፖለቲካ አቅጣጫ ባሻገር ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጋር በጋራ ጥቅምና በተለያዩ የትብብር መስኮች የትብብር አቅም እየጎለበተ መምጣቱን ያመላክታል።
ኢትዮጵያ መጪውን የኮፕ-32 (COP-32) ፕሬዝዳንትነት ስትረከብ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በግንባር ቀደምትነት እንደምታራምድ መጠቆሟም ቁርጠኝነቷን ያሳያል። ለመድረኩ ስኬትም ከኮፕ-31 (COP-31) ፕሬዝዳንት ጋር በትብብር ትሰራለች።
የአራቱም ማዕዘናት ዓለም እንግዶችም ቀጣይ ዓመት ለኮፕ-32 ጉባኤ የታሪክ ማኅደር፣ የገናና ሥልጣኔ፣ የአሸናፊዎች፣ የሰው ልጆችና ቡና መገኛዋ ምድረ ቀደምት ኢትዮጵያ ይተማሉ። ኢትዮጵያም እንግዶቿን ለመቀበል ቁርጠኛ ዝግጅት እያደረገች ነው።
ቀጣናዊ ትስስርና ጉርብትናን ማጠናከር
የመደመር መንግሥት ቅድሚያ ለጎረቤት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ዕጣ ፈንታ በጋራ ልማትና በመሠረተ ልማት እንዲተሳሰሩ ዕድል ፈጥሯል። በዚህም ኢትዮጵያ ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳን እና ከደቡብ ሱዳን ጋር በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ በመንገድ እና በመገናኛ መሠረተ ልማቶች በመተሳሰር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን በተግባር አረጋግጣለች። የፖሊሲው ሌላኛው ትሩፋት "ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ" የሚለውን መርህ በመከተል በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት አስተዋጽኦ አበርክታለች፤ በማበርከትም ላይ ትገኛለች።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መጽሐፍ ከጎረቤት ሀገራት ትኩረት የሚሰጥ የውጭ ግንኙነት ሐተታ ላይ፤ በውጭ ግንኙነታችን ውስጥ የመጀመሪያው ትኩረታችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን መመሥረትና ማጠናከር ይሆናል። ጎረቤት ሀገራትን በተመለከተ “ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል” ወይም “ምንጭን የተጠጋ ዋርካ፣ ሁልጊዜ እንደረካ” የሚለውን ነባር መርሕ መከተል ያስፈልገናል።
ሉዓላዊነትንና ብሔራዊ ፕሮጀክቶችን በዲፕሎማሲ ማስጠበቅ
የመደመር መንግሥት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሀገርን ሉዓላዊነትና የመልማት መብት የማስጠበቅ በተግባር የተፈተነ ጠንካራ አቅም ገንብቷል። ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የፈጠረችው የከሸፈ ዓለም አቀፍ ጫናም ሁነኛ አብነት ነው። ይህም የተዛቡ ትርክቶችን በሰከነ የዲፕሎማሲ አካሄድ በማረም የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት በተግባር አረጋግጧል። የታላቁ ሕዳሴ በረከትም ከኢትዮጵያውያን የጎጆ ብርሃን የተሻገረ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ አቅም ፈጥሯል።
የመደመር መንግሥት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በአንድ አቅጣጫ የዲፕሎማሲ አካሄድ የተገደበ አይደለም። ኢትዮጵያ ከምዕራቡም ከምሥራቁ ዓለም ጋር ሚዛናዊነትን የጠበቀ ግንኙነት መመሥረቷ ዓለም አቀፍ ተሰሚነትና ተፈላጊነቷን በእጅጉ አሳድጓል። በዚህም ዘርፈ ብዙ ዓለም አቀፍ አጋርነትና የብሪክስ (BRICS) አባልነትን እንድታረጋግጥ አስችሏታል።
ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ ታላላቅ ኢኮኖሚዎች ስብስብ የሆነውን ብሪክስን በሙሉ አባልነት መቀላቀሏ፣ በዓለም አቀፍ የፖለቲካና የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ያላትን ድምፅ ከማሳደጉ በተጨማሪ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የምታደርገው ያላሰለሰ ጥረት ዓለም አቀፍ ቅቡልነት እያገኘ መጥቷል።
ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት
የመደመር መንግሥት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ውጤታማነት አዎንታዊ ሚና እንዲኖረው ተደርጎ ተቃኝቷል። ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ለተደረጉ ግንኙነቶችና ስምምነቶች፣ የዕዳ ሽግሽግ ድርድሮች እና በግብርና፣ በማዕድን፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፎች ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የፖሊሲው የቀጣይ ዘመን ስትራቴጂያዊ ዕድሎች
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ሦስት አስርት ዓመታትን በተሻገረ የጎልማሳ ዕድሜ የታጠረ የብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ነው። የወቅቱ አንገብጋሚ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታሪክን ከሕግ፣ መልክዓ ምድራዊ ቅርበትን ከተፈጥሮ፣ አዳጊ የሕዝብ ቁጥርን ከፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር አሰናስሎ የያዘ የሕልውና አጀንዳ ነው።
የመደመር መንግሥት የውጭ ግንኙነት የዲፕሎማሲ አካሄድም የኢትዮጵያን የባሕር በር የሕልውና ጥያቄ ዓለም እንዲገነዘብ አስችሏል። በዚህም ጥያቄው ከቅቡልነት ወደ እንዴት ይፈጸም ተሸጋግሯል። የውጭ ግንኙነት ፖሊሲውም የኢትዮጵያ ሰላማዊና በሰጥቶ መቀበል የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተውን የባሕር በር ጥያቄ ፍትሐዊና ምክንያታዊ ቅቡልነት መሰረት አስይዟል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተፈጠረው ቀጣናዊ የኢኮኖሚና የኃይል ትስስርም የኢትዮጵያን የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የገለጠ ተምሳሌት ነው። የብሪክስ እና የደቡብ-ለደቡብ ትብብርን በመጠቀም ጥገኝነትን መቀነስና ሰፊ የልማት ፋይናንስ አማራጮችን ማስፋት አስችሏል። የአየር ንብረት ዲፕሎማሲና የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋቶች ለዓለም አቀፍ ግንኙነቷ እንደ ትልቅ አቅም የሚያገለግሉ ሲሆን፤ አዲስ አበባን የላቀ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲና የኮንፍረንስ ማዕከል ለማድረግ ሁሉን አቀፍ ልማቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የመደመር መንግሥት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ኢትዮጵያን ከተከላካይነት ወደ አጀንዳ ቀርጾ ሰጪነት፣ ከተናጠል ጉዞ ወደ ቀጣናዊ ትስስር ያሸጋገረ ውጤታማ ፖሊሲ ነው። የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጭነት በመሸጋገር ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቅ ከፍታ መጓዙን ቀጥሏል። ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት የዲፕሎማሲ ዕድሎች ለቀጣይ ዘመን ድል ጠንካራ መሠረት ናቸው።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የዓለም የልብ ምት ናት። የዓለም አቀፉ የኮፕ-32 መድረክ ታዳሚያንም ኢትዮጵያ በልባቸው እያሰናሰሉ ነው። ትልቅ ሀገር፣ የትልቅ ሕዝብ መኖሪያና ታላቅ ርዕይ የሰነቀችው ኢትዮጵያም እንግዶቿን በብቃት ሞሽራ ለማስተናገድ ከወዲሁ ሽርጉዱን ጀምራለች።
ኑ የሰው ልጅና የቡና መገኛ፣ አረንጓዴ ዐሻራና የዘመናዊ ከተማ ግንባታ፣ የአሸናፊዎችና የጥንታዊ ሥልጣኔ ማማ፣ የዲፕሎማሲ ማዕከልና የአፍሪካ የወደፊት የንጹሕ ኃይል ማዕከሏ ኢትዮጵያ ዘመን አይሽሬ ትውስታን በልብዎ ይቅረጹ እያለች ትጠራላች - ኢትዮጵያ!