ቀጥታ፡

አሰባሳቢ ትርክትን መገንባት ለዜጎች አንድነትና አብሮነት መሰረት ነው - የሃይማኖት መምህራንና አባቶች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊነት አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ለዜጎች አንድነትና አብሮነት መሰረት መሆኑን የተለያዩ የሃይማኖት መምህራንና አባቶች ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ!!

ኢትዮጵያ በሺህ ዘመናት ዑደት ዜጎቿ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ሕብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን በመጠበቅ፣ ሀገራቸውን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያስተላልፉ የኖሩባት የብዝኃ ጸጋዎች ምድር ናት።

የአደባባይ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላትም ከዚህ ታሪካዊ የአብሮነት እሴት የሚመነጩ፣ የዜጎችን መተሳሰብ፣ መከባበርና አንድነት በማጎልበት ጉልህ ስፍራ የሚይዙ አሰባሳቢ መድረኮች ናቸው።

የመደመር መንግሥትም የዜጎችን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች እንደ የጋራ ጸጋና ሀብት በመውሰድ ሕብረ ብሔራዊ ወንድምና እህትማማችነትን የሚያጎለብት አስተሳሳሪ የጋራ ትርክት ለመገንባት እየሰራ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የነገረ መለኮትና ሥነ ልቦና ከፍተኛ መምህር አባ ጌዴዎን ብርሃነ ለኢዜአ እንዳሉት፣ አክብሮትና ትብብር የእምነታችን መገለጫ ነው።

ሃይማኖታዊ አስተምህሮን መሠረት በማድረግም የዜጎችን መንፈሳዊና ዓለማዊ አብሮነትና አንድነት የሚያጎለብት ትምህርተ ወንጌል እየተሰጠ ነው ብለዋል።

በዚህም ቤተ ክርስቲያኗ ምዕመኖቿ በሀገራዊ ሕብረ ብሔራዊነት ውስጥ አንድነትን በማጎልበት የሀገርን ሰላምና ልማት እንዲያስቀጥሉ ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኗን ገልጸዋል።

በቀጣይም ሁሉም ዜጋ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ለሀገራዊ የጋራና አሰባሳቢ ትርክት ግንባታ፣ ለአንድነትና ለዕድገት ገንቢ ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የአወሊያ የእርዳታና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሃጂ ሰኢድ አስማረ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ሀገር ናት ብለዋል።

የኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊነትም ለሀገር አንድነት፣ ሰላምና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

የእምነት አስተምህሮ ሰላምና አንድነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን ታሳቢ በማድረግም፣ በዜጎች መካከል አንድነትና መተባበርን የሚያጎለብት ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብዝኃነት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና አንድነትን በማጎልበት፣ አሰባሳቢ ትርክት ግንባታን የሚያጠናክር እሴት እያነጸ መሆኑን አንስተዋል።

ዜጎችም ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም የበኩላቸውን ገንቢ ሚና በመወጣት፣ የተሻለች ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በሕብር ያሸበረቁ ዜጎች በአንድነትና በመተሳሰብ የሚኖሩባት ሀገር ናት ያሉት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዝዳንት ቄስ ደረጀ ጀምበሩ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም የዜጎችን አንድነትና አብሮነት በማጎልበት፣ የተሻለች ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ ጉልህ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በሃይማኖታዊ አስተምህሮም የዜጎችን አብሮነትና ሀገራዊ አንድነት የሚያጎለብት ትምህርት በመስጠት፣ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ የጋራ አቋም እንዲይዙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊነትም አሰባሳቢና የጋራ ትርክትን በመገንባት፣ ጉልህ ትርጉም ያለው የአንድነት መሠረት መሆኑን አመላክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም