የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ከድንገተኛ የሕክምና ወጪና የኢኮኖሚ ጫና ታድጎናል -- በድሬዳዋ ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ከድንገተኛ የሕክምና ወጪና የኢኮኖሚ ጫና ታድጎናል -- በድሬዳዋ ተጠቃሚዎች
ድሬዳዋ፤ ህዳር 9/2019 (ኢዜአ)--በድሬዳዋ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች በሁሉም የሕክምና ተቋማት የተሟላ የጤና አገልግሎት ማግኘታቸው ከድንገተኛ የሕክምና ወጪና የኢኮኖሚ ጫና እንደታደጋቸው ገለጹ።
በድሬዳዋ አስተዳደር በገጠር እና በከተማ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ በመምጣቱ ፍትሃዊ የጤና ተደራሽነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ተችሏል።
በስተዳደሩ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የጤና መድህን በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ አስችሏል።
በገንደቆሬ ጤና ጣቢያ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ከነበሩት መካከለ አቶ ስዩም በቀለ እንዳሉት፤ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በሁሉም ደረጃ ባሉ የጤና ተቋማት የሕክምና አገልግሎት እያገኙ ነው።
ከዚህ በፊት የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የገንዘብ ዕጥረት እንደነበረባቸው አስታውሰው፣ የጤና መድህን አባል በመሆናቸው በማንኛውም ወቅት ያለችግር መታከም መቻላቸውን ተናግረዋል።
ቤተሰቦቻቸውም ሕመም ሲገጥማቸው ከጤና ጣቢያ ጀምሮ አስከ ሆስፒታል ደረስ በቅብብሎሽ የፈለጉትን ሕክምና ማግኘታቸው ጤናቸውን በአግባቡ ለመጠበቅና አምራች ለመሆን እንዳስቻላቸው ነው የገለጹት
የጤና መድህን አገልግሎት ከሰጠን እፎይታ ባለፈ ጤናማና አምራች እንድንሆን እያገዘን ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ተጠቃሚ አቶ አብደላ ሙሜ ናቸው።
በአዲስ ከተማ ጤና ጣቢያ ሲታከሙ ከነበሩት የጤና መድህን ተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ አስራት ወልደፃዲቅ እና አቶ ቢኒያም አበራ የጤና መድህን አባል መሆናቸው የዓመታት ችግራቸውን እንደፈታላቸው ተናግረዋል።
አልፎ አልፎ በጤና ተቋማት ከሚያጋጥም የመድኃኒት እጥረት ችግር በስተቀር በቅብብሎሽ አስከ ከፍተኛ ሆስፒታል ድረስ በመሄድ መታከም መቻላቸው የኢኮኖሚ ጫና እንዳቃለለላቸው ገልጸዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ከተጀመረ ወዲህ በድሬዳዋ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በማስፋት ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተቻለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በአስተዳደሩ ጤና ቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አስተባባሪ ሲስተር ሜሪ አምዴ ናቸው።
በአሁን ወቅት በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መታቀፍ ካለባቸው 91 በመቶዎቹ ተካተው አስፈላጊውን የሕከምና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት በተለይ ከፍለው መታከም የማይችሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች ከችግር መታደጉን የገለጹት አስተባባሪዋ፣ የህብረተሰቡን የእርስ በእርስ መረዳዳትና ትስስርን እያጠናከረ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም የጤና መድህን አባላትን ቁጥር በማብዛት የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ከማሳደግ ባለፈ ጤናማ እና አምራች ዜጋ የመፍጠር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።