ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ሀገራዊ አቅሞችንና ዓለምአቀፍ ትብብሮችን በማቀናጀት ወረርሽኞችን ቀድሞ የመከላከል አቅሟን እያጎለበተች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ሀገራዊ አቅሞችንና ዓለምአቀፍ ትብብሮችን በማቀናጀት ወረርሽኞችን ቀድሞ የመከላከል አቅሟን እያጎለበተች ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ሀገራዊ አቅሞችንና ዓለምአቀፍ ትብብሮችን በማቀናጀት ወረርሽኞችን ቀድሞ የመከላከል እና ከተከሰተም ፈጥኖ የመቆጣጠር አቅሟን እያጎለበተች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
21ኛው ዓለም አቀፍ የፓንዳሚክ ፈንድ ቦርድ ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ሀገራዊ አቅሞችንና ዓለምአቀፍ ትብብሮችን በማቀናጀት ወረርሽኞችን ቀድሞ የመከላከል እና ከተከሰተም ፈጥኖ የመቆጣጠር አቅሟን እያጎለበተች ትገኛለች ብለዋል።
የበሽታዎች ቅኝት፣ የላቦራቶሪ አቅምንና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ዝግጁነትን ለማሳደግ ያለመ "የኢትዮጵያ ወረርሽኝ ዘርፈ-ብዙ መከላከል ዝግጁነት እና ምላሽ ፕሮጀክት" በስፋት እየተተገበረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የጤና፣ የግብርና እና የገንዘብ ሚኒስቴሮች እንዲሁም ዓለምአቀፍ ተቋማትን በጋራ ያስተሳሰረ መሆኑን አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ድንገተኛ የጤና አደጋዎችንና ወረርሽኞችን በራሷ አቅም ቀድማ ለመከላከል እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የምታደርገውን ጥረት እያገዘ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሰው እና የእንስሳት ላቦራቶሪዎችን በካርታ የመለየት፣ መመሪያዎችን የማዘጋጀት እና የበሽታ አምጪ ተህዋስያንን ዘረ-መል የመመርመር አቅምን እንደሚያሳድግም ጠቁመዋል።
በሺዎች ለሚቆጠሩ የዘርፈ-ብዙ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት የተሳሳቱ መረጃዎችን መመከት የሚያስችል የአደጋ ጊዜ ተግባቦት ስርዓት በመዘርጋት ህብረተሰቡን የመጠበቅ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የጤናው ዘርፍ ስራዎች በብቸኝነት ሳይሆን ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ አጋሮች እንዲሁም ማህበረሰቡን በማቀናጀት በማስተባበር እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
የጤና አጠባበቅ ስርዓትን ለማጠናከር በላቦራቶሪዎች አቅም ግንባታ፣ በሰለጠነ የሰው ሃይል ዝግጅት፣ በድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሰጪዎች ስልጠና እንዲሁም በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶች ላይ ሰፊና አስተማማኝ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የተከናወኑ የጤና ስራዎች ውጤታማና አበረታች መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ የማይበገር የጤና ስርዓት እየገነባች መሆኑን አመላክተዋል።