ኢትዮጵያ የገነባችው የመከላከያ ሰራዊት አቅም ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ትልቅ አቅም ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የገነባችው የመከላከያ ሰራዊት አቅም ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ትልቅ አቅም ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2019(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት የገነባችው የመከላከያ ሰራዊት አቅም ሀገራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ትልቅ አቅምና ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑን በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ገዛኸኝ ፈቃዱ ገለጹ።
የመደመር መንግሥት የሀገርን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለማቆም ካከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች መካከል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን በአዲስ መልክ ማደራጀትና ማዘመን ዋነኛው ነው።
ሰራዊቱን ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት በማላቀቅ ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን በብቃት የሚወጣ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትም ተከናውነዋል።
በዘመናዊ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል ስልጠናና በተቋማዊ አደረጃጀት ረገድ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት የሰራዊቱን የመፈጸምና የመከላከል አቅም ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረውታል።
ይህ በመደመር መንግሥት የተገነባው ጠንካራና ዘመናዊ ወታደራዊ አቅም የኢትዮጵያን ሰላም ከማስጠበቅ ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ዋስትና እንደሆነ ያነጋገርናቸው የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች ገልጸዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ገዛኸኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ሰራዊቷን በከፍተኛ ሁኔታ በማደራጀት፣ በስልጠናና በአቅም ግንባታ የማድረግ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ ገንብታለች።
በሀገር ውስጥ የተፈጠረው ይህ ጠንካራ ወታደራዊ አቅም ሀገራዊ ሰላምን ከማስፈን ባለፈ፣ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተሳትፎና ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድገው ጠቁመዋል።
ሰራዊቱ ይህንን የገነባውን አቅም በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በእውቀት ይበልጥ በማጠናከር በሰላም ማስከበር ዘርፍ ያለውን የመሪነት ሚና ማስቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ የፖሊሲና ስትራቴጂ ጉዳዮች ቡድን መሪ ሌተናል ኮሎኔል አራጋው ገብረመድህን በበኩላቸው፣ መከላከያ ሰራዊቱ በቴክኖሎጂ፣ በስልጠናና በሰው ኃይል ቁጥር እየዘመነ መምጣቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከኮሪያ እስከ አፍሪካ ሀገራት ድረስ በሰላም ማስከበር የካበተ ታሪክ እንዳላት ያስታወሱት ሌተናል ኮሎኔል አራጋው፣ አሁን የተገነባው ዘመናዊ የሰራዊት አቅም ሰላምን ከሀገር ውስጥ አልፎ ለጎረቤት ሀገራትና ለዓለም ለማስጠበቅ ሙሉ ብቃት እንዳለው አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን የሰላም ማስከበር አስተዋጽኦና የሰራዊቱን አቅም በጥናትና በመጽሐፍ በመሰነድ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።