በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን የቱሪዝም መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን የቱሪዝም መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሮቤ ህዳር 09/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን የተፈጥሮ፣ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ የጎብኝዎች ቁጥርና የዘርፉ ገቢ እያደገ መምጣቱን የዞኑ ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ባለፈው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቱሪስቶች አካባቢውን የጎበኙ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓመት ደግሞ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶችን በመሳብ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገባቷል።
የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የሶፍ ኡመር ዋሻ፣ ድሬ ሼህ ሁሴንና ሌሎች በርካታ የተፈጥሮ፣ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች መገኛ በመሆኑ በሀገሪቱ የቱሪዝም እምቅ አቅም ካላቸው አካባቢዎች አንዱ ነው።
በተለይም የባሌ ተራሮች ልዩ የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳርና የዱር እንስሳት ሀብት፣ የሶፍ ኡመር ዋሻ ልዩ የተፈጥሮ ገጽታና የድሬ ሼህ ሁሴን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች አካባቢውን ለቱሪዝም ልማት ምቹ ከሚያደርጉት ዋና ዋና ሀብቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ደጀኔ ሚልኬሳ እንዳሉት፤ በዞኑ የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን ለማልማት፣ መሠረተ ልማቶችን ለማሻሻልና የአካባቢውን የቱሪዝም አቅም በስፋት ለማስተዋወቅ በተለያዩ መስኮች ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው።
ባለፈው የበጀት ዓመት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቱሪስቶች አካባቢውን የጎበኙ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓመት ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶችን በመሳብ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
መስህቦችን ማልማት የጎብኚዎችን ቁጥር ከማሳደግ ባለፈ የአካባቢውን ነዋሪዎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማጠናከር፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የባህልና ታሪካዊ ቅርሶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።
የባሌና አካባቢው የተለያዩ ሥነ-ምህዳሮች፣ የተፈጥሮ ሀብቶችና ታሪካዊ ቅርሶች በአንድ አካባቢ መገኘታቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፤ እምቅ የቱሪዝም ኃብቱን ለማጎልበት ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዞኑ ከ100 በላይ አዳዲስ የተፈጥሮ፣ ታሪካዊና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም መስህቦች በጥናት መለየታቸውንና ለመስህቦቹ ዲጂታል ካርታ መዘጋጀቱንም በማሳያነት አንስተዋል።
የመስህብ ስፍራዎችን በምርምር መለየት፣ መመዝገብና የጎብኚዎችን መረጃ ተደራሽ ማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በዞኑ ሰሞኑን የቱሪዝም መስህቦችን የጎበኙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ቡድንም የአካባቢውን እምቅ ሀብት ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።
በመስክ ጉብኝቱ የሚዘጋጁ የዜና ዘገባዎች፣ ፎቶግራፎችና የቪዲዮ ምስሎች የመስህብ ስፍራዎቹን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ይዘት በስፋት በማሳየት የጎብኚዎችን ፍላጎት ለማነሳሳት ያግዛሉ ነው ያሉት።
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝም ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ገረመው መብራቱ እንዳሉት፣ ፓርኩን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የጎበኙ ሲሆን ከዚህም የተሻለ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
በፓርኩ ውስጥ በርካታ ሐይቆች እንደሚገኙ የጠቆሙት ኃላፊው፣ ከእነዚህም ውስጥ ብዙዎቹ ክረምት ከበጋ የማይደርቁ ቋሚ ሐይቆች መሆናቸው ልዩ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል።
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የጎበኙት ዴቪድ ማርሻል፣ ከዚህ በፊት በተለያየ ሀገር የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችን የጎበኙ ቢሆንም በባሌ ባዩት እምቅ የቱሪዝም ሀብት ግን እጅግ መደነቃቸውን ገልጸዋል።
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ማራኪ እና በየትኛውም ቦታ የማይገኝ ውብ ተፈጥሯዊ ገጽታ ያለው መሆኑን አንስተዋል።