የሰሊጥ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እና የጤና ጸጋዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሰሊጥ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እና የጤና ጸጋዎች
የሰሊጥ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እና የጤና ጸጋዎች
ሰሊጥ በዓለም ላይ ካሉ የቅባት እህሎች አንዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የሰብሉ መገኛና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋነኛ አምራችና ላኪ ሀገር ነች። በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ "ነጭ ወርቅ" በመባል የሚታወቀው ሰሊጥ፣ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ከመሆኑም ባለፈ ለሰው ልጅ ጤናና ስነ-ምግብ ያለው ጠቀሜታ እጅግ የላቀ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የሰሊጥ ሰበል ሞቃታማና ከፊል-ደረቅ የአየር ንብረት የሚፈልግ ሰብል ሲሆን ከ25° ዲግሪ ሴልሺየስ እስከ 35°ዲግሪ ሴልሺየስ ባለው የሙቀት መጠን ውስጥ በተሻለ ሁኔታ ያድጋል። ለሰሊጥ ከዓመታዊ የዝናብ መጠን አንጻር ከ450 እስከ 650 ሚሊ ሜትር ዝናብ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ሰብሉ ድርቅን የመቋቋም አቅም ያለው በመሆኑ አነስተኛ ዝናብ ባለባቸው አካባቢዎችም ይለማል። ሰሊጥ በባህሪው ሞቃታማና ከፊል ቆላማ አካባቢዎችን የሚወድ ሲሆን፣ ከባህር ጠለል በላይ ከ500 እስከ 1,250 ሜትር ከፍታ ባላቸው አካባቢዎች በስፋት ይበቅላል።
የግብርና ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ውኃ አዘል፣ ለስላሳ እንዲሁም የሸክላና የአሸዋ ቅልቅል ያለው አፈር ለሰሊጥ ልማት እጅግ ተስማሚ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ለሰሊጥ ልማት እጅግ ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረትና ሰፊ ለም መሬት አላት። በኢትዮጵያ ሰሊጥ በዋናነት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል ሁመራ፣ መተማ፣ ቋራ፣ አርማጭሆ እና ጎንደር ዙሪያ እንዲሁም ምዕራብ ኦሮሚያ ፣ ጋምቤላና ፓዌ የሚጠቀሱ ናቸው። በኢትዮጵያ በየዓመቱ በሰሊጥ ልማት የሚሸፈነው መሬት እንደየአየር ሁኔታውና ወቅታዊ ሁኔታዎች ቢለዋወጥም በአማካይ ከ500,000 እስከ 600,000 ሄክታር ይደርሳል።
የኢትዮጵያ ሰሊጥ ልማት በአብዛኛው በዝናብ ላይ የተመሰረተ ሲሆን በአነስተኛ የአርሶ አደር መሬትና በሰፋፊ የግል እርሻዎች ላይ ይከናወናል። ይሁን እንጂ ሰሊጥ ሲደርስ የመበተን ባህሪ ስላለው ምርቱን በወቅቱ በሰው ኃይል መሰብሰብ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል። የአየር ንብረት መዛባት፣ የተባይ ስርጭትና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እጥረት በሰሊጥ ልማት የሚስተዋሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ናቸው። ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ ሰሊጥ አምራች አካባቢዎች ምርቱን በኮምባይነር ታግዞ የመሰብሰብና የመውቃት ልምድ እየጎለበተ መምጣቱ ችግሩ እየተቃለለ እንዲመጣ አድርጎታል።
ሰሊጥ ባለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሬ በተጨማሪ ለሥራ ዕድል ፈጠራም ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ከምርት ዝግጅት ጀምሮ እስከ ማቀነባበር፣ ማሸግ እና ንግድ ድረስ በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ያገኙበታል። በተለይም በምርት ስብሰባ ወቅት ለሚሰማሩ ጊዜያዊ ሠራተኞች ትልቅ የገቢ ምንጭ ነው። ከዚህም ባሻገር ለምግብ ዘይት ማምረቻዎች እና ለተለያዩ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ዋነኛ ግብአት ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኘው ዓመታዊ የሰሊጥ ምርት እንደየዓመቱ የዝናብ ሁኔታ የሚለያይ ቢሆንም በአማካይ ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል አካባቢ እንደሚደርስ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከአጠቃላይ የሰሊጥ ምርት ውስጥ አብዛኛው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሲሆን የሀገር ውስጥ ፍጆታ በጣም አነስተኛ ነው። በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም ከፊት ከሚገኙ የሰሊጥ ላኪ ሀገራት አንዷ ናት። ሰሊጥ በኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ውስጥ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ቁልፍ ሰብል ነው። ከዚህም የተነሳ ነጭ ወርቅ እየተባለ ሲጠራም ይስተዋላል። ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ ቀዳሚ የሰሊጥ ላኪ ሀገራት ተርታ ወስጥ ነው የምትመደበው። ምርቱ በዋናነት የሚላከውም ወደ ቻይና፣ እስራኤል፣ ቱርክ፣ ጃፓንና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ነው።
የሰሊጥ ልማት ከዘር እስከ አጨዳና መውቂያ ድረስ ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚጠይቅ በመሆኑ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
ሰሊጥ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ካለው ጠቀሜታ አንጻር በሀገር ውስጥ ለሚገኙ የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካዎች፣ ለዳቦ ቤቶችና ለጣፋጭ ምግብ አምራቾች እንደ ግብአት ሆኖ ያገለግላል።ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ሰሊጥን በጥሬው ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ (ለምሳሌ ታሂኒ እና የሰሊጥ ዘይት በማምረት) ወደ ውጭ የመላክ ጥረቶች ተጀምሯል።
ሰሊጥ ከምግብነት አንጻር ያለው ፋይዳ በተመለከተም ሰብሉ በንጥረ-ነገር የበለጸገ በመሆኑ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ውስጥ ይካተታል። ሰሊጥ ከ45% እስከ 55% የሚደርስ ከፍተኛ የቅባት (ጤናማ ስብ) ይዘት ያለው ሲሆን፣ በፕሮቲን (20 እስከ 25%)፣ በፋይበር፣ በካልሲየም፣ በብረት (Iron)፣ በማግኒዚየም፣ በዚንክ እና በቫይታሚን "B" እና "E" የበለጸገ ነው።
ከምግብነት አኳያ በኢትዮጵያ ባህላዊ አመጋገብ ሰሊጥ ተቆልቶና ተፈጭቶ በተለያየ መልክ ለምግብነት ይውላል። በተለይም በጾም ወቅት ዋነኛ የፕሮቲንና የኃይል ምንጭ ነው። በዳቦ፣ በኩኪስና በተለያዩ ጣፋጭ ምግቦች ላይ ሲነሰነስም ለምግቡ ልዩ ጣዕምና መዓዛ ይሰጣል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰሊጥ ተፈጭቶ "ታሂኒ" (Tahini) የተባለ ለምግብ ማጣፈጫነት የሚያገለግል ክሬም ይሰራበታል፤ እንዲሁም "ሃልቫ" (Halva) ለተሰኘው ጣፋጭ ምግብ ዋና ግብዓት ነው። የሰሊጥ ዘይት ለምግብ ማብሰያነትና ለሰላጣ ማጣፈጫነት እጅግ ተመራጭ ነው።
ከሕክምናና ጤና አንጻር ያለው ጠቀሜታ በተመለከተም ሰሊጥ በውስጡ በያዛቸው ልዩ ፀረ-ኦክሲዳንቶች ማለትም ሴሳሚን እና ሴሳሞሊን አማካኝነት ለተለያዩ የጤና እክሎች መከላከያና መድኃኒትነት ሆኖ ያገለግላል። በዚህም ሰሊጥ የልብ ጤናን ይጠብቃል። በተለይ በውስጡ የሚገኙት ጤናማ ቅባቶች በደም ውስጥ ያለውን ጎጂ ኮሌስትሮል (LDL) በመቀነስ የልብ ህመምንና የደም ቧንቧ መጥበብን ለመከላከል ጠቀሜታ አላቸው። ሰሊጥ በማግኒዚየም የበለጸገ በመሆኑ የደም ቧንቧዎችን በማስፋት ከፍተኛ የደም ግፊትን ለመቀነስነና ለመቆጣጠር ይረዳል።
በውስጡ የያዘው ከፍተኛ መጠን ያለው ካልሲየም፣ ፎስፈረስ እና ዚንክ ለአጥንት እድገትና ጥንካሬ ወሳኝ ነው። በጤና ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዕድሜ መግፋት ምክንያት የሚመጣን የአጥንት መሳሳት ይከላከላል። እንዲሁም የምግብ መፈጨት ሥርዓትን ያስተካክላል። በፋይበር የበለጸገ በመሆኑ የሆድ ድርቀትን ከመከላከል ባለፈ የአንጀት ጤናንም ይጠብቃል።
በተለይ ጥቁር ሰሊጥ በብረት (Iron) ማዕድን የበለጸገ በመሆኑ ቀይ የደም ሴሎችን ለማምረትና የደም ማነስን ለመከላከል ይረዳል። እንዲሁም የስኳር በሽታን በመቆጣጠር በኩል ሚናው የላቀ ነው። ዝቅተኛ የካርቦሃይድሬትና ከፍተኛ የፕሮቲንና ጤናማ ስብ ይዘት ስላለው በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ሚዛን ለመጠበቅ ይረዳል። በተጨማሪ የሰሊጥ ዘይት ቆዳን ለማለስለስ፣ ከፀሐይ ጨረር ለመከላከልና ቁስልን ቶሎ ለማዳን በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ የመዋቢያ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል።
የኢትዮጵያ ሰሊጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው ተፈላጊነት አንጻር ምርታማነትን በዘመናዊ ግብርና ማሳደግና እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ መላክ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ያሳድገዋል። በሀገር ውስጥም አጠቃቀሙን ማስፋትና ዜጎችም ሰሊጥን በምግባቸው የመጠቀም ባህላቸውን ማሳደግ ለጤናና ስነ-ምግብ መሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
በመሆኑም ልማቱን በማስፋፋትና በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማዋል የሚደረጉ የተቀናጁ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።