ቀጥታ፡

ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ፤ ከታሪካዊ የአየር ንብረት የፍትሕ ጥያቄ እስከ ኮፕ-32 ጉባኤ ዝግጅት

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ!!

የዘመናችን ፈታኝና ዐበይት ክስተት እየሆነ የመጣ የአየር ንብረት ለውጥ ሳይንሳዊ መሰረቱም ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ የተሻገረ ታሪክ አለው። ለዚህም በ19ኛው ክፍለ ዘመን የሙቀት መጠበቂያ ጋዞች (Greenhouse Gases) በምድር ሙቀት ሚዛን ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ የሚመለከቱ ሳይንሳዊ ጥናቶች ተጀምረዋል። በተለይም የኢንዱስትሪ አብዮት በአውሮፓ ከተስፋፋ በኋላ የድንጋይ ከሰል፣ የነዳጅና የጋዝ አጠቃቀም መጨመር፣ የደን ጭፍጨፋና ከኢንዱስትሪ የሚወጡ የካርበን ልቀት የዓለምን የአየር ንብረት ስርዓት ቀስ በቀስ እየበከሉት መጥተዋል።

የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ቀውስ በኢንዱስትሪ ከበለፀጉ ሀገራት የሚመነጭ ቢሆንም የችግሩ ገፈት ቀማሾች ዝቅተኛ የኢኮኖሚና አደጋውን የመላመድ አቅማቸው አነስተኛ የሆኑ ታዳጊ ሀገራት መሆናቸው ጉዳቱን የከፋ ያደርገዋል። የሰዎችን ስደት በማባባስ የምግብ ዋስትናን፣ የጤና ሥርዓት፣ የውሃ አቅርቦትና መሰል ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል።

በተለይም የአፍሪካ ቀንድ አርሶና አርብቶ አደር፣ የባሕር ዳርቻና የደሴት ሀገራት፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎች፣ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አዛውንቶችና አካል ጉዳተኞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዋስትና ቅርቃር ውስጥ በመክተት ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ያስከትላል። በቅርቡ በኔፓል የተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የምስራቅ አፍሪካ የኤልኒኖ ድርቅ፣ በላቲንና ሰሜን አሜሪካ፣ በእስያና ሌሎች ሀገራት የሚከሰቱ አውሎ ነፋሶችና የእሳት አደጋዎች የአየር ንብረት ለውጥ ላይ አፋጣኝ መፍትሔ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አመላካች ናቸው።

ለዚህም በካርበነ ልቀት ቅነሳ መርህ የታዳሽ ኃይል ማስፋፋት፣ የንጹህ ትራንስፖርት ማበረታታት፣ የደን ጥበቃና የካርቦን ልቀት በመቀነስ የለውጥ መላመድ ምኅዳርን የሚያጎለብቱ የድርቅ መቋቋም ግብርና፣ የውሃ አስተዳደር፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትና አደጋ መቋቋም የሚችል የመፍትሔ አቅጣጫ ስልቶችን መገንባት ያስፈልጋል። የኪሳራና ጉዳት ካሳ (Loss and Damage)፣ የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የአቅም ግንባታ ስልቶችም የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ መሰረታውያን ናቸው።

የአየር ንብረት ዲፕሎማሲም በአንድ ጊዜ የተፈጠረ ሳይሆን በሳይንሳዊ ምርምር፣ በዓለም አቀፍ ውይይትና በሕጋዊ ስምምነቶች የተገነባ ረጅም ሂደት ነው። እ.አ.አ ከ1979–2026 በተለያዩ ሀገራት ከተሞች የተካሄዱት ዓለምአቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ መድረኮችም የሂደቱን ታሪካዊ የጉዞ ምዕራፎች ያመላክታሉ።

በዚህም እ.ኤ.አ. 1979 በጄኔቫ ስዊዘርላንድ የመጀመሪያው የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ ሳይንሳዊ ግንዛቤን ለማሳደግ ሁነኛ መሰረት ጥሎ ያለፈ መድረክ ነበር። እ.ኤ.አ. በ1988 በጄኔቫ የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተጠሪ ቡድን (IPCC) በመመስረቱም ዓለምአቀፍ ሳይንሳዊ ግምገማ ለማካሄድ ተቋማዊ መሰረትን ፈጥሯል።

በብራዚሏ ሪዮ ዴ ጄኔሮ እ.ኤ.አ. 1992 የጸደቀው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነትም (UNFCCC) ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ቀውስ መፍትሔ የሚያመላክት የሕግ መሰረት ጥሏል። በጀርመን መዲና በርሊንም እ.ኤ.አ. 1995 የመጀመሪያው የስምምነት ወገኖች ጉባኤ (COP1) ተካሂዷል።

በጃፓን ኪዮቶ እ.ኤ.አ. 1997 የተካሄደው 3ኛው የስምምነት ወገኖች ጉባኤ (COP3) የኪዮቶ ፕሮቶኮልን በማፅደቅ የካርበን ልቀት ቅነሳ ግዴታዎችን ወደ ዓለምአቀፍ ስምምነት አምጥቷል። በሞሮኮ ማራካሽ እ.ኤ.አ. 2001 የተካሄደው 7ኛው የስምምነት ወገኖች ጉባኤ (COP7) የኪዮቶ ፕሮቶኮል ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችሉ ደንቦችን አስጸድቋል።

በዴንማርክ ኮፐንሃገን እ.ኤ.አ. 2009 የተካሄደው 15ኛው የስምምነት ወገኖች ጉባኤ (COP15) አዲስ ዓለምአቀፍ የአየር ንብረት ስምምነት ለመፍጠር ታላቅ ጥረት የተደረገበት ታሪካዊ መድረክ ነበር። በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ እ.ኤ.አ. 2015 የተካሄደው 21ኛው የስምምነት ወገኖች ጉባኤም (COP21) የፓሪስ ስምምነትን በማፅደቅ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ትብብር አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

በዩናይትድ ኪንግደም ግላስጎው እ.ኤ.አ. 2021 የተካሄደው 26ኛው የስምምነት ወገኖች ጉባኤ (COP26) የግላስጎው የአየር ንብረት ስምምነትን በማፅደቅ የዓለም አቀፍ የልቀት ቅነሳ ጥረቶች እንዲጠናከሩ አድርጓል። በግብፅ ሻርም ኤል ሼክ እ.ኤ.አ. 2022 የተካሄደው 27ኛው የስምምነት ወገኖች ጉባኤ (COP27) በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሚደርሱ ኪሳራና ጉዳቶች የሚውል ፈንድ ለመመስረት ታሪካዊ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በዱባይ እ.ኤ.አ. 2023 ያስተናገደችው 28ኛው የስምምነት ወገኖች ጉባኤ (COP28) የፓሪስ ስምምነትን የመጀመሪያ ዓለምአቀፍ የአፈጻጸም ግምገማ (Global Stocktake) አከናውኗል። እ.ኤ.አ. 2024 በአዘርባጃን ባኩ የተካሄደው 29ኛው የስምምነት ወገኖች ጉባኤ (COP29) በአዲስ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ፋይናንስ ግብ ላይ ታሪካዊ ውሳኔን አሳልፏል።

እ.ኤ.አ. 2025 በቤለም ብራዚል የተካሄደው 30ኛው የስምምነት ወገኖች ጉባኤም (COP30) የአማዞን ደን ጥበቃንና የአየር ንብረት ቃል ኪዳኖችን ወደ ተግባር የማሸጋገር አጀንዳን በማስቀደም ታሪካዊ ምዕራፍ አስመዝግቧል። የዘንድሮው 31ኛው የስምምነት ወገኖች ጉባኤም (COP31) የቱርክዬን አስተናጋጅነት ከአውስትራሊያ የድርድር አመራር ጋር በማጣመር በአንታሊያ ተካሂዷል። ኢትዮጵያም ታሪካዊውን ዓለምአቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ መድረክ በ2027 በአዲስ አበባ 32ኛው የስምምነት ወገኖች ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ  ቅብብሎሹን በአንታሊያ ተረክባለች።

መድረኩን በብቃት ለማስተናገድ ቀደም ብላ መዘጋጀት ጀምራለች። 32ኛውን የኮፕ ጉባኤ እንደ ሀገር ያስመዘገበቻቸውን እመርታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ ተነሳሽነቶች ለዓለም የምታሳይበት ሁነኛ ጉባኤ ይሆናል። በዚህም የኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ (Cradle of Humanity)፣ የቡና መገኛ (Origin of Coffee)፣ አረንጓዴ ዐሻራ (Green Legacy)፣ ጥንታዊ ስልጣኔ (Ancient Civilization)፣ አዲስ አበባና ከተሜነት፣ የዲፕሎማሲ ማዕከል (Diplomatic Hub)፣ የአሸናፊዎች ምድር (Land of Champions) እንዲሁም የታዳሽ ኃይል (Clean Energy) ልማት ስምንት ብሔራዊ የገጽታ ግንባታ ጭብጦች ጎልተው ይገለጣሉ።

በሰው ልጅ የመጀመሪያው ፍጥረት የዘር ሀረግ አመጣጥም በኢትዮጵያ መሆኑን ሚሊዮን ዓመታት ዕድሜን በማስቆጠር በአፋር ክልል የተገኙት የሉሲ እና ሰላም ቅሪተ አካልም ሕያው የታሪክ ምስክሮች ናቸው። የቡናን ታሪክ ከጥንታዊ ደኖቿ በማፍለቅ ከሺህ ዘመናት በፊት ጀምሮ ማጣጣም የጀመረችው ኢትዮጵያ ዛሬም ድረስ ለወደፊት የሚሻገር የዓለም የቡና ባህል ሥርዓትና የጣዕም ሃብት ምንጭ ናት።

በጥንታዊ ሥልጣኔና ቅርስ በኩልም ከአክሱም ሐውልቶች እስከ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ከኃይማኖታዊ ቅርሶች እስከ ባሕላዊ እሴቶች ድረስ የሺህ ዘመናት ሥልጣኔ ኢትዮጵያን ተምሳሌት አድርገዋታል። በአዲስ አበባ የተከናወነው እና እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ የከተማ ልማትም የአሁኑ ትውልድ የራሱን የሥልጣኔ ታሪክ ዐሻራ በማሳረፍ ውብ፣ ጽዱና ኢትዮጵያን የሚመጥን የከተሜነት ምኅዳር እየገነባ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ መርሃ ግብር የአረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት የሚያስችል መሰረት እየጣለ ነው። በውሃ፣ በነፋስ፣ በጸሐይ፣ በጂኦተርማልና ሌሎች አማራጮች ከሀገር ውስጥ የተሻገረ የኤሌክትሪክ ሀይል ለምስራቅ አፍሪካ በማቅረብ አፍሪካዊት የታዳሽ ኃይል ማዕከል የሚያሰኟትን አመርቂ ውጤቶች አስመዝግባለች።

በፓን-አፍሪካ እሳቤም ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ቀንዲል፣ የአንድነት ተምሳሌትና የኩራት ምንጭነቷን ምስጋና ለቅድመ አያቶችና በዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች በተግባር አስመስክራለች። ጀግኖች አትሌቶች በዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ ደግመው ደጋግመው የተጎናጸፉት ደማቅ የአሸናፊነት ድል ስምና ዝናዋን በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጓል።

በአጠቃላይ በእነዚህ የታሪክ፣ የሥልጣኔና የአረንጓዴ ልማት ትሩፋቶች ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ እና ታላቅ ርዕይ የሰነቀችው ኢትዮጵያ በአዲስ አበባው የኮፕ-32 ጉባኤ በታሪካዊ ገድልነት በጉልህ የምታሳያቸው የብሔራዊ ኩራት ማኅደሮች ናቸው። በዚህም በአፍሪካ ተምሳሌትነቷን ለዓለም በማረጋገጥ ለሀገራዊ ገጽታ ግንባታ፣ ለአየር ንብረት ዲፕሎማሲ የበላይነት እንዲሁም ለዓለም ሀገራት በተሞክሮነትና በመልካም ልምድነት በኩራት በማቅረብ የዲፕሎማሲ ከፍታዋን ይበልጥ ታጸናለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም