ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ ኢኮኖሚውን የሚያጎለብት ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሐረር፤ ህዳር 09/2019 (ኢዜአ)፦ የሐረሪ ክልልን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ የኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የክልሉ ኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።

በሐረሪ ክልል ምጣኔ ሀብቱን በዘላቂነት ለማሳደግ የአምራች ኢንዱስትሪውንና የኢንቨስትመንት ዘርፉን በስፋት የማነቃቃት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። 

የክልሉ መንግሥት የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ የአሠራር ሥርዓቶችን በማዘመን፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦትን በማሻሻልና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። 

በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በአገልግሎትና በሆቴል ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚደረገው ድጋፍና ማበረታቻ የኢንቨስትመንት ፍላጎቱን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጎታል።

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 51 አልሚዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱም የዚሁ ጥረት አንዱ ማሳያ ነው። 

እነዚህ ፕሮጀክቶች ወደ ሙሉ ትግበራ ሲገቡም በክልሉ ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ፣ የምርትና አገልግሎት አቅርቦትን በማሳደግ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግሩታል ተብሎ ይታመናል።

የክልሉ ኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ  ምክትል ሃላፊ አቶ ሰሚር አብዱላሂ እንዳገለጹት፤ ቢሮው የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ ኢኮኖሚውን የሚያጎለብትና የሥራ ዕድል ፈጠራን የሚያጠናክሩ  ተግባራት እያከናወነ ነው።

በክልሉ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ውጤታማና ቀልጣፋ አሰራርን በመዘርጋት ለአዳዲስ አልሚዎች የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት በተደረገው ጥረት፤ በሩብ ዓመቱ ባጠቃላይ ለ51 አልሚዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን  ገልጸዋል።

ፈቃዱ ከተሰጣቸው አልሚዎች 12ቱ በሆቴል፣ ዘጠኙ በማኑፋክቸሪንግ  ሲሆኑ ቀሪዎቹ  በግብርናና በሌሎች ዘርፍ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ጠቅላላ የካፒታል መጠናቸውም ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ገልጸዋል።

በክልሉ ከዚህ ቀደም ፈቃድ ወስደው የነበሩ  ፕሮጀክቶች በሩብ ዓመቱ ወደ ማምረትና አገልግሎት መስጠት በመሸጋገር ለዜጎች  ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደፈጠሩም ጠቅሰዋል።

በክትትልና ቁጥጥር ተግባራት  በ58 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ የእርምት እርምጃዎች መወሰዳቸውን  ጠቁመዋል።

በዚህም 15 ፕሮጀክቶች የቃል ማስጠንቀቂያ፣ 26 የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 10 ፕሮጀክቶች እገዳ የተጣለባቸው ሲሆን፤ የሰባት ባለሀብቶች ፕሮጀክቶች ደግሞ ፈቃዳቸው መሰረዙን አስታውቀዋል።

በክልሉ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚደረገው ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ምክትል ቢሮ ሃላፊው  አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም