ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችንበዘላቂነት ለመከላከል ወሳኝ መፍትሄ ነው - ምሁራን

ሀዋሳ፤ ሕዳር 9/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመከላከል ወሳኝ መፍትሄ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በዘርፉ የላቀ ውጤት አስመዝግባለች።

ሀገሪቱ የተራቆቱ መሬቶች ወደ ቀደመ ይዞታቸው እንዲመለሱ በማድረግና የታዳሽ ሀይል አማራጮቿን በማስፋት ለአረንጋዴ ልማት እና እድገት ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራም ኢትየጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ከችግር ተናጋሪነት ወደ መፍትሄ አመንጪነት በመሸጋገር ለአፍሪካና ለዓለም ምሳሌ የሚሆን ተግባር አከናውናለች።

በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተቀባይነት እንዲያድግ በማድረጉ እ.አ.አ በ2027 የሚካሄደውን 32ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን እንድታዘጋጅ ተመርጣለች። 

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራንም እውቅናው የኢትዮጵያ በዘርፉ ተግቶ የመስራት ውጤት መሆኑን አንስተው፣ እንደ ሀገር እየተመዘገበ ያለውን ውጤት በቀጣይም አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፀጋዬ በቀለ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት ያከናወነቻቸው የአረንጓዴ አሻራ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በርካታ ውጤቶችን አስገኝተዋል።

በተለይ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ ባህል እየጎለበተ መምጣት እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ካለው ፋይዳ ባለፈ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እያስቻላት ነው ብለዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ጸጋዬ ገለጻ፣ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የደን ሽፋንን በማሳደግ፣ የአፈር ለምነትን በመመለስና የውሃ አካላት አቅምን በማሳደግ ለኢኮኖሚ መሰረት የሆነውን ግብርና ውጤታማነት እያሳደገ ነው።

ከዚህም ባለፈ ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ በመስኖ ልማት ዓመቱን ሙሉ በማምረት ዜጎች የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡና በኢኮኖሚም ተጠቃሚ እንዲሆኑ አግዟል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመከላከል ወሳኝ መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የምግብ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ስነ-ምግብ ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር ከበደ አበጋዝ በበኩላቸው እንዳሉት፣ እንደሀገር የተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት በስነምግብ ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል።

በተለይ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተተከሉ ችግኞች የመሬት ለምነትና የውሃ አቅምን በመጨመር የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ በሥርአተ ምግብ ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸዋል። 

ይህም ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብን ለመፍጠር እያገዘ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ኢትዮጵያ በተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ ያከናወነቻቸው ተግባራት ለሌሎች ምሳሌ እንዳደረጋትም ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቋቋም አቅም ፈጥሯል ያሉት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጂኦግራፊና አካባቢ ጥበቃ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ምስራቅ ታምሬ (ዶ/ር) ናቸው።

የተራቆቱ አካባቢዎች በደን መሸፈናቸው የደረቁ ምንጮች መልሰው እንዲያገግሙና የአፈር መሸርሸርን በማስቀረት ለእርሻ ሥራ ውጤታማነት የላቀ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብለዋል።

ይህም ዜጎች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት አበርክቶው የላቀ መሆኑን ነው ያነሱት።

ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሸራ መርሀግብር የተከናወኑ ተግባራት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመቋቋም ፋይዳቸው የጎላ መሆኑነም አመልከተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም