ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የየሀገራቸውን ሁለንተናዊ የትብብር አድማስ በማስፋት የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ለማጎልበት እንሰራለን -የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2019(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና የየሀገራቸውን ሁለንተናዊ የትብብር አድማስ በማስፋት የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ለማጎልበት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ከአፍሪካ፣ እስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓና ካሪቢያን ሀገራት በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙ የ16 ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ በትላንትናው እለት ተቀብለዋል።

በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት በክብር ዘብና በማርሽ ባንድ ደማቅ ሥነ-ሥርዓት ታጅቦ በተካሄደው መርሐ ግብር በኢትዮጵያ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ የሰሜን ኮሪያ፣ የቆጵሮስ፣ የቼክ ሪፐብሊክ እና የአየርላንድ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤቸውን ለፕሬዝዳንቱ አቅርበዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሕንድ፣ የቻድ ሪፐብሊክ፣ የኦስትሪያ፣ የኖርዌይ፣ የፊንላንድ ሪፐብሊክ፣ የማልታ ሪፐብሊክ፣ ጣሊያን፣ የባርቤዶስ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ የሉክሰምበርግና የግሬናዳ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝዳንቱ አቅርበዋል።

የሹመት ደብዳቤቸውን ለፕሬዝዳንቱ ካቀረቡት መካከል ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ አምባሳደሮች እንዳሉት፤ የኢትዮጵያና የየሀገራቸውን ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ትብብርና ግንኙነት በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ይሰራሉ።

በኢትዮጵያ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አምባሳደር አብደላ ሀሰን ኡባይድ ሀሰን አልሻምሲ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ጥልቅ ወዳጅነት የገነቡ ስትራቴጂክ አጋር ሀገራት ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አምባሳደር በመሾማቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው በመጥቀስ፤ በቆይታቸው የሀገራቱን የትብብር ብሩህ አድማስ በማስፋት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት ጠንካራ ግንኙነት ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የቆጵሮስ አምባሳደር ሳቫስ ቪላድሚሩ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቆጵሮስ አምባሳደር ሆኜ በመሾሜ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።

በቀጣይም በኢትዮጵያና በቆጵሮስ መካከል የባህል፣ የንግድና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማጎልበት የሀገራቱን ኢንቨስትመንት ለማጠናከር በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያና በቼክ ሪፐብሊክ መካከል በመንግሥት ለመንግሥትና በሌሎች ዘርፎች ጠንካራ የዲፕሎማሲ ትብብር እየተገነባ ነው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ያን ሮቼክ ናቸው።

የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትም በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የፕሮጀክት ግንባታ ትብብር የበለጠ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ኪያራን ማደን በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በተሰጣቸው ሹመትና ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ፈጣን ዕድገት በመደገፍ የአየርላንድ አልሚ ባለሀብቶች በተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች የሚሰማሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በሌላ መልኩም በቅርቡ የሀገራቱን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር በባህል ዘርፍ ትኩረቱን ያደረገ ሁነት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ዴቪሽ ዑታም በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያና ሕንድን ታሪካዊና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ወዳጅነት የበለጠ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያን ፈጣንና አስደናቂ ዕድገት የሚያሳልጥ የንግድና ኢንቨስትመንት የኢኮኖሚ ትብብርን ለማጎልበት ይሰራል ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ፒተር ኤልስነርማካይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም