ታዳጊ አትሌቶች የኢትዮጵያን የድል ጉዞ የሚያድሱ ሀገራዊ ኩራቶች ናቸው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ታዳጊ አትሌቶች የኢትዮጵያን የድል ጉዞ የሚያድሱ ሀገራዊ ኩራቶች ናቸው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ኅዳር 9/2019 (ኢዜአ)፦ታዳጊ አትሌቶች የኢትዮጵያን የድል ጉዞ የሚያድሱ ሀገራዊ ኩራቶች መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ታዳጊ አትሌቶቹን በአካል አግኝተው ማበረታታቸውን ገልጸዋል።
ታዳጊዎቹ በአፍላ ዕድሜያቸው በዓለም መድረክ ባሳዩት ብቃትና ባስመዘገቡት ድል የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በክብር ከፍ አድርገዋል ነው ያሉት።
ይህ ውጤት ለመላው ኢትዮጵያውያን ደስታና ኩራት፣ ለታዳጊው ትውልድ ደግሞ ታላቅ ተስፋና ተምሳሌት መሆኑንም ተናግረዋል።
የተመዘገበው ወቅታዊ ድል ለነገው የላቀ ስኬት መነሻና መሠረት መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አትሌቶቹ በራሳቸው በመተማመን፣ ህልማቸውን በማሳደግና ከዛሬው ድል የበለጠ ከፍታን በማለም ለመጪዎቹ የዓለም ሻምፒዮናዎችና ኦሎምፒክ ጨዋታዎች በበለጠ ብቃት፣ ትጋትና ቁርጠኝነት እንዲዘጋጁ አሳስበዋል።
መንግሥት በቀጣይ የስኬት ጉዟቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉንም ዓይነት ድጋፍ እንደሚያደርግ ያረጋገጡት አቶ ተመስገን፤ አትሌቶቹ ብቃትና ችሎታቸውን በቀጣይነት እያዳበሩ የሀገራቸውን ስምና ሰንደቅ በዓለም አደባባይ በተከታታይ ከፍ ለማድረግ በጽናት ለድል እንዲሰለፉ አደራ ብለዋል።