ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም ረጅም ዕድሜ የሚያገለግሉ የኮንክሪት መንገዶች ለመገንባት የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም ረጅም ዕድሜ የሚያገለግሉ የኮንክሪት መንገዶች ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር ጋር በመተባበር "የኢትዮጵያ መንገድ ዘርፍ ልማት የሲሚንቶ ኮንክሪትን ለመንገድ ንጣፍ መጠቀም ያሉ ዕድሎች" በሚል መሪ ሃሳብ አውደ ጥናት አካሂዷል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ምርምር ማዕከል የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር አስተባባሪ ኢንጂነር ይታገሱ ደሳለኝ በዚህ ወቅት፤ የመንገድ መሰረተ ልማት የሀገር ዕድገት መሰረት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የተተገበሩ የመንገድ ዘርፍ ልማት መርሃ ግብሮች የከተማና ገጠር ትስስርን በማጎልበት ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የመንገድ ደኅንነትን የሚያረጋግጥ የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ልማት በማስፋት አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮች በሥራ ላይ እንደሚውሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች ረጅም ዕድሜ የሚያገለግል የኮንክሪት መንገድ ፕሮጀክት መገንባት የሚያስችል በቂ አቅም መፍጠራቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያን የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቁጥርና የማምረት አቅም ዕድገት ታሳቢ በማድረግም የመንገድ መሰረተ ልማትና ኢንዱስትሪ ትስስርን ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር የቦርድ ሊቀ-መንበር አዱኛ በቀለ በበኩላቸው፤ የሲሚንቶ ኮንክሪት የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።

ይህም ኢትዮጵያ በቴክኒክና በኢኮኖሚ የተመጣጠነ፣ ዘላቂና ተወዳዳሪ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ አማራጭን ለመፍጠር እንደሚያስችላት አንስተዋል።

የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ረጅም ዕድሜ በማገልገል ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የልማት ዘርፍ ነው ያሉት ደግሞ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ታሪኩ አለማየሁ ናቸው።

ለዚህም የኢትዮጵያን የሲሚንቶ ኮንክሪት የመንገድ መሰረተ ልማት ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ የማምረት አቅማቸውን በማሳደግ ግብዓት እንደሚያቀርቡ አረጋግጠዋል።

የደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኃይሌ አሰግዴ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ጊዜ የመንገድ መሰረተ ልማት ትስስር ለማስፋት በርካታ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል።

የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ንጣፍ በውሃና ዝናብ በቀላሉ የማይበላሽና ረዥም ዕድሜ ያለው አማራጭ መሰረተ ልማት መሆኑንም አስረድተዋል።

የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ለአስፋልት ግንባታ ከውጭ የሚገባን ግብዓት የሚያስቀር አማራጭ ዘርፍ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮንሳልቲንግ ማኅበር የቦርድ አባል ኢንጂነር ሮቤል መርኪያ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም