የኢትዮጵያ የዘመኑ ሉዓላዊነት በምግብ ራስን በመቻልና በዲጂታል አቅም ይረጋገጣል - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዘመኑ ሉዓላዊነት በምግብ ራስን በመቻልና በዲጂታል አቅም ይረጋገጣል - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የዘመኑ ሉዓላዊነት በምግብ ራስን በመቻልና በዲጂታል አቅም ይረጋገጣል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
ዘመናዊ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን (Modern neo colonialism) ለመታገል የተቋቋመው “ለሕዝቦች ነፃነት!” ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ጠቅላላ ጉባዔ በሩሲያ ሞስኮ እየተካሄደ ነው።
በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
አቶ አደም ፋራህ በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ በብሔራዊ ሉዓላዊነት፣ በልማት የራስን በራስ የመወሰን ነፃነት (Development Autonomy) እና እየተለዋወጠ በመጣው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥርዓት ዙሪያ ያላትን አቋም እና ምልከታ አቅርበዋል።
በንግግራቸውም ኢትዮጵያ ለብሔራዊ ሉዓላዊነት፣ ለሀገራት እኩል ክብር እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር እና በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ለተመሠረተ ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ዳግም አረጋግጠዋል።
በንግግራቸውም ኢትዮጵያ ለብሔራዊ ሉዓላዊነት፣ ለሀገራት እኩልነት፣ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተርና በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ የተመሠረተ ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ ሥርዓት እንዲኖር ያላትን ጽኑ አቋም አፅንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
በዓድዋ ድል ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛትን በመመከት እና የሕዝቦችን ነፃነትና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በማስከበር ረገድ ያላትን የቆየ ታሪካዊ ቅርስ አስታውሰዋል።
አክለውም በዘመናችን ሉዓላዊነት አዳዲስ ወቅታዊ ፈተናዎችን መቋቋምን እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።
በዚህም ረገድ ኢትዮጵያ በምግብ ራስን በመቻል፣ በዲጂታል እና በመረጃ (ዳታ) አስተዳደር፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በኢኮኖሚ ብዝኃነት እና በተቋማዊ ማሻሻያዎች አማካኝነት ስትራቴጂካዊ ነፃነቷን (Strategic Autonomy) ለማጠናከር እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
በተጨማሪም ሀገሪቱ ሀብቷንና አቅሟን በማስተባበር ዘላቂና በራስ አቅም ላይ የተመሠረተ ልማት ለማረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ግዙፍ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች እየተገበረች ይገኛል ነው ያሉት።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርን፣ የስንዴ ልማትን፣ የከተማ ኮሪደር ልማትን እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባሻገር ውጤታማ የባለብዙ ወገን ትብብር (Multilateralism)፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የአፍሪካ ፍትሐዊ ውክልና መረጋገጥ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረጉ ዓለም አቀፍ አጋርነቶች እንዲሁም ሰላምና እርቅ ለጋራ ብልጽግና መሠረት መሆናቸውን ነው ያስገነዘቡት።
ብልጽግና ፓርቲ የጉባኤው ተሳትፎ ከዲፕሎማሲያዊ ውክልና ባለፈ፤ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ አጋርነቶችን ለማጠናከር፣ እንዲሁም በሉዓላዊነት፣ በኒዮ-ኮሎኒያሊዝም፣ በልማት ነፃነት እና ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ ሥርዓትን በመገንባት ዙሪያ በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውይይቶች ላይ የኢትዮጵያን አቋም ለማስረጽ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
በጉባዔው የምልዓተ ጉባዔ ውይይቶች፣ የክብ ጠረጴዛ ምክክሮች እና የሁለትዮሽ ንግግሮች እየተደረጉ ሲሆን፤ በማጠቃለያውም የውሳኔ ሐሳቦችና ስትራቴጂካዊ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ይፈረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ብልጽግና ፓርቲ በዚህ ተሳትፎው አማካኝነት የፖለቲካ ምክክሮችን ወደ ተጨባጭ ዓለም አቀፍ ትብብር ለመቀየር፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርስና ወቅታዊ የልማት ተሞክሮ ለማስተዋወቅ እንዲሁም እየተለዋወጠ ባለው ዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ የሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ለማስከበር እንደሚሰራ ገልጿል።