ቀጥታ፡

15ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፍረንስና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019 (ኢዜአ)፦15ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፍረንስና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ እንደሚካሂድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሀብራቢ አስታወቁ።

ሚኒስትር ያስሚን ወሀብራቢ ሁነቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ መድረኩ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር ጋር የሚዘጋጅ ነው።

"የማይበገር ንግድ እና ዘላቂ የእሴት ሰንሰለቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የሚካሄደው መድረክም ህዳር 15 እና 16 ቀን 2019 ዓ.ም ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ አስታውቀዋል።

በመድረኩ ከ17 ሀገራት የተውጣጡ ዓለም አቀፍ ገዢዎችን ጨምሮ ከ600 በላይ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑ ተናግረዋል።

በኮንፍረንሱ ከ100 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምርት ማቅረብ የሚያስችልና ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የንግድ ለንግድ (B2B) ስምምነት ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

ከ15 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎች በሚቀርቡበት መድረክ ተሳታፊዎችም የኢትዮጵያን ብሔራዊ የጥራት መንደርና የልማት ሥራዎች የሚጎበኙበት መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ከ555 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የጥራጥሬና ቅባት እህል ምርቶች ወደ ውጭ በመላክ 570 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በወጪ ንግድ ላይ ያስገኘውን ከፍተኛ ውጤት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኤደኦ አብዲ በበኩላቸው፤ መድረኩ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን የሚያጎለብት የገበያ ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል ወሳኝ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የፋይናንስ ተደራሽነትን፣ የሎጂስቲክስ አቅርቦትንና እሴት ሰንሰለቶችን ለማሳደግ ከዓለም ባንክ፣ ከብሔራዊ ባንክ እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ይህም የሀገር ውስጥ አምራቾችንና ላኪዎችን ከዓለም አቀፍ ገዢዎች ጋር በቀጥታ በማገናኘት የንግድ ውሎችን ለማስፋት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም