የአየር ንብረት ፋይናንስ ለታዳጊ ሀገራት ቅድሚያ ፍላጎቶች ምላሽ በሚሰጥ መልኩ ሊቀርብ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረት ፋይናንስ ለታዳጊ ሀገራት ቅድሚያ ፍላጎቶች ምላሽ በሚሰጥ መልኩ ሊቀርብ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019 (ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ፋይናንስ ለታዳጊ ሀገራት ቅድሚያ ፍላጎቶች ምላሽ በሚሰጥ መልኩ ሊቀርብ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከኮፕ 31 ጎን ለጎን በተካሄደው “ከውጥን ወደ ተግባር፡ በዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም (Global Environment Facility - GEF)፣ በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ፈንድ (Least Developing Countries Fund - LDCF) እና በልዩ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ (Special Climate Change Fund - SCCF) አማካኝነት የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ” በተሰኘው የከፍተኛ ኃላፊዎች ውይይት ላይ ንግግር አድርገዋል።
ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ ለታዳጊ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍና የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ሀገራዊ ውጥኖችን ወደ ተግባር ለመቀየር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ሀብቶች በቂ በማይሆኑበት ጊዜ ትግበራ እንደሚዘገይ፣ ተጋላጭነት እንደሚባባስ እና በጋራ ጥረት ላይ የሚኖረው እምነት እንደሚዳከም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ኮፕ 32ትን በአዲስ አበባ ለማስተናገድ ዝግጅት ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት፣ በዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም ድጋፍን ጨምሮ በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ፈንድ (LDCF) እና በልዩ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድን (SCCF) ለማጠናከር የተጀመረውን የሀብት ማሰባሰብ ጥረት በደስታ እንደምትቀበል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከሁሉም አጋሮች ጋር ለመሥራት ያላትን ዝግጁነት ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።