ኢትዮጵያ ፍልሰተኞችን እንደ ልማት አጋርና የኢኮኖሚ ተዋናይ በመቁጠር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ፍልሰተኞችን እንደ ልማት አጋርና የኢኮኖሚ ተዋናይ በመቁጠር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ፍልሰተኞችን እንደ ልማት አጋርና የኢኮኖሚ ተዋናይ በመቁጠር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ ገለጹ።
በፍልሰት ጉዳዮች ላይ ያተኮረው አራተኛው የአፍሪካ የግሉ ዘርፍ ፎረም (AFD 2026) በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
"ቀጣዩ ምዕራፍ፤ ይበልጥ አካታች የሆነ የኢኮኖሚ ሥነ-ምህዳር መፍጠር" የፎረሙ መሪ ቃል ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ ፍልሰተኞችንና ተፈናቃዮችን እንደ ዕድገት አጋርና የኢኮኖሚ ተዋናይ የሚመለከት የልማት አቅጣጫ መከተል እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህም በሰብአዊ ድጋፍ ፈላጊነትና በተጋላጭነት ብቻ መታየት እንደሌለባቸው የገለጹት አምባሳደር ሀደራ፣ ያላቸውን ክህሎት፣ ዕውቀት፣ የሥራ ፈጠራ አቅምና ምርታማነት መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ ራሳቸውን እንዲችሉ ከማገዙም በላይ፣ የቀጣናውን ገበያ እንደሚያጠናክርና የማምረት አቅምን እንደሚያሳድግ አመልክተዋል።
ይህም ለተፈናቃዮች ብቻ ሳይሆን ለተቀባዩ ማህበረሰብም ሰፊ የኢኮኖሚ ሽግግርና የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያመጣም ነው ያብራሩት።
ኢትዮጵያ ለፍልሰተኞች ጥበቃና ዘላቂ መፍትሔ ያላትን ቁርጠኝነት የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የስደተኞች አዋጅ ቁጥር 1110/2019 መብታቸውን፣ የሥራ፣ የትምህርትና የመዘዋወር ነጻነትን የማስፋት ስራ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም መንግሥት የሥራ ዕድሎችንና የሥራ ፈቃዶችን ለማስፋት፣ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥን ለማቀላጠፍ፣ ብሔራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም የስደተኞችን ጉዳይ በሀገር አቀፍና በአካባቢ የልማት ማዕቀፎች ውስጥ ለማካተት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በዝርዝር አስረድተዋል።
የግሉ ዘርፍ ሚና የማይተካ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ሀደራ፣ ከማህበራዊ ኃላፊነት ባለፈ በንግዱ ዘርፍ አዋጭ በሆነና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ አጋርነት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካን የኢኮኖሚ አካታችነት አጀንዳ ለማሳካት የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ዕድል መቀየር፣ የግል ካፒታልና አዳዲስ የፋይናንስ አማራጮችን ስራ ላይ ማዋል፣ የስደተኞችን የሥራ ፈጠራና የገበያ ትስስር ማጠናከር፣ በክህሎትና በሥራ ዕድል ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንዲሁም አካታች የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ልማትን ማስፋፋት እንደሚገባም ነው ያነሱት።
ለዚህም መንግሥታት፣ የንግድ ተቋማት፣ የፋይናንስ ተቋማትና የልማት አጋሮች የኢንቨስትመንት መሰናክሎችን ለማስወገድ በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ፎረም የሥራ ዕድልን የሚያሰፉ፣ በስደተኞች የሚመሩ ድርጅቶችን የሚያጠናክሩ እንዲሁም የፋይናንስና የገበያ ተደራሽነትን የሚያሻሽሉ ተግባራዊ አጋርነቶች፣ ተጨባጭ የኢንቨስትመንት ቃል ኪዳኖችና ሊተገበሩ የሚችሉ ምክረ-ሐሳቦች ይመነጫሉ እንደምትጠብቅ አምባሳደሩ ገልጸዋል።
የዚህ ፎረም (AFD 2026) ስኬት የሚለካው በተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች፣ በተጠናከሩ የንግድ ተቋማት፣ በተጨባጭ ኢንቨስትመንቶችና በተለወጡ የሰዎች ሕይወት መሆን እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፎረሙ ከ400 በላይ ልዑካንን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና ዓለም አቀፍ አጋሮችን በአንድ መድረክ አገናኝቷል።
መድረኩ በመላው አፍሪካ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጠናከር የመፈናቀል ችግርን በዘላቂነት ለመፍታትና የኢኮኖሚ አካታችነትን ለማረጋገጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የሚመሰረትበትና የሐሳብ ልውውጥ የሚደረግበት አህጉራዊ መድረክ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።