ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ቁጥራቸው ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ይከተባሉ

አርባ ምንጭ፤ ሕዳር 8/2019 (ኢዜአ)--በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት እንደሚከተቡ የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ክልል አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ምንተስኖት መልካ (ዶ/ር) እንዳሉት ክልል አቀፍ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በሁለት ዙር ይሰጣል።

የመጀመሪያ ዙር የክትባት ዘመቻ ከሕዳር 12 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀናት እንደሚሰጥ ገልጸው፣ ሁለተኛው ዙር ከአንድ ወር በኋላ እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።

ቤት ለቤት በመሄድ በሚሰጠው የክትባት ዘመቻ ከዚህ በፊት ክትባት የወሰዱና ያልወሰዱ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕጻናትን ለመከተብ መታቀዱንም አመልክተዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሠራዊት ዲባባ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የፖሊዮ በሽታን ማስወገድ ካልተቻለ በሁለንተናዊ ልማት ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል።

የፖሊዮ በሽታን ለማጥፋት በሚደረገው ዘመቻ መገናኛ ብዙሃን ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን መረጃ በወቅቱ በማድረስ የበኩላቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።

የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ሃላፊ በርገኔ በቀለ በበኩላቸው የፖሊዮ በሽታን መከላከል የሚቻለው ሕጻናትን በመደበኛው የክትባት መርሃ ግብርና በዘመቻ በሚሰጥ ክትባት በመሆኑ ለዘመቻው መሳካት በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም