ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ተቋማዊ አቅሟንና አጋርነቷን በማጎልበት በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2019(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ተቋማዊ አቅሟንና አጋርነቷን በማጎልበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የሰላም ማስከበር ሚና ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ተቋማዊ አቅሟን በማዘመን፣ የሰራዊቷን ዝግጁነት ማሳደግና ቀጣናዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ አጋርነቷን በማስፋት በዓለም የሰላም ማስከበር ሚናዋን እንደምትወጣም አክለዋል።

የኢፌዴሪ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ማሠልጠኛ ተቋምና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ በጋራ ባዘጋጁት መድረክ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ስርዓት ለውጥና በባለብዙ ወገን ትብብር መዳከም ተግዳሮቶች ውስጥ የሰላም ማስከበር ሚናዋን የምታስቀጥልባቸው ስትራቴጂዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ እንዳሉት የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተሳትፎ የዓለም አቀፍ ግዴታ ብቻ ሳይሆን የሚያኮራ ብሔራዊ ታሪክና ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ሀብት ነው።

ኢትዮጵያ በ1950ዎቹ በኮሪያ ጦርነት ከተሳተፈችበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ከ70 በላይ ዓመታት ውስጥ ከ180 ሺህ በላይ የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በማሰማራት ለዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ያላትን ጽኑ አቋም በተግባር ማሳየቷን አንስተዋል።

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተቋማዊ አቅምን ማዘመንና ፖሊሲዎችን፣ የህግ ማዕቀፎችንና የአሰራር ስርዓቶችን ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር ለማጣጣምም እንዲሁ ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል።

ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እና ከምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጋር ያለው ትብብር እንደሚጠናከርና ዘላቂ የሀብት ምንጮችን ለማስፋት ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን የወደፊት የሰላም ማስከበር ስትራቴጂ ከዓለም አቀፍ ግዴታ፣ ከአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ከሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ደህንነት ጥቅሞች ጋር በማቀናጀት እንደሚመራም ተናግረዋል።

ከመድረኩ የተገኙ ምክረ-ሃሳቦች በአግባቡ ተሰንደው የሚመለከታቸው ተቋማት በቅንጅት በመስራት ወደ ተጨባጭ ፖሊሲና ተግባራዊ መርሃ-ግብር እንዲቀይሩትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም